ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “የሶማሊያ መንግስት ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮነነ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ማምሻውን “በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ” ዙሪያ በሰጠው መግለጫ “የሶማሊያ መንግስት ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል ተችቷል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ “በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል” ያለው መግለጫው “ቀጠናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል” ሲል አስታውቋል።

ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየቷን እና ከሁለት ቀናት በፊት ነሃሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ወታደሮች እና መሳሪያዎች የጫኑ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተያዘው ወር መጀመሪያ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ወደ ካይሮ በማቅናት ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር መገናኘታቸውን እና ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሶማሊያ የሚሰፍሩት የግብጽ ወታደሮቹ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ ማለትም በጌዶ፣ በሂራን እና በባይ ባኮል ስፍራዎች ላይ እንደሚሰፍሩ እየተገለጸ እንደሚገኝም በዘገባችን ተካቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ማምሻውን በሰጠው መግለጫ “ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ሲል አቋሙን አንጸባርቋል።

“ይህም በመሆኑ በቀጣናው የብሄራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች ትገኛለች” ሲል አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያለውን ወቅታዊ አለመግባባት ለመፍታት እንዲያስችል በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይም በንቃት ተሳትፎ አድርጋለች ሲል ያስታወቀው መግለጫው “የሶማሊያ መንግስት እነዚህን ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል ተችቷል።

በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሰላም ተልዕኮ የማዘጋጀት እና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ በቀጠናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ አገራትን ተገቢ የሆኑ ስጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡

“ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞከሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል” ሲልም አስጠንቅቋል።

“ቀደም ሲል አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም” ሲልም አስታውቋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button