ዜናህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የሶማሌ ክልል የምክር ቤት አባል የነበሩት ጁዌሪያ መሐመድ ቤተሰቦች ተገቢውን ፍትህ አለማግኘታቸውን ገለጹ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2016 ዓ/ም፦ በጅግጅጋ ከተማ አየር ማረፊያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ አባል በጥይት ተመተው የተገደሉት የሶማሌ ክልል የምክር ቤት አባል እና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ጁዌሪያ መሐመድ ቤተሰቦች ተገቢውን ፍትህና ካሳ አለማግኘታቸውና በክልሉ ጸጥታ አካላት ተጽዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ። 

የጁዌሪያ ቤተሰቦች “ተገቢው ፍትህ እና ካሳ አለማግኘታችን ሳያንስ በክልሉ ጸጥታ ኃይሎች ማስፈራሪያ፣ ድብደባና እስር እየደረሰብን ነው” ሲሉ ገልጸዋል። 

ጥቅምት15/ 2015 ዓ.ም የክልሉ የምክር ቤት አባሏ ጁዌሪያ የተገደሉት ከውጭ አገር የመመጡትን እህታቸውን ለመቀበል በሶማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ በሚገኘው ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ ባመሩበት ወቅት በፌዴራል ፖሊስ አባል በተከፈተባቸው ተኩስ ነበር። 

በተከፈተባቸው ተኩስ ከ13 ዓመት ታዳጊ ልጃቸው ጋር ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከአሜሪካ የመጡት የጁዌሪያ እህት አያን መሓመድ በሶስት ጥይት እግራቸውን ሲመቱ ልጃቸውና የክልሉ የካቢኔ አባል የሆኑት አብዲራሺድ መሀመድን ላይ የመቁሰል አደጋ አድርሷል።

በዕለቱ በተፈጸመው ጥቃት በሶማሌ ክልል ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩት የምክር ቤት አባልና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጁዌሪያ ወድያው ህይወታቸው ሲያልፍ እህታቸው አያን ላይ በደረሰው ጉዳት በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም አንደኛው እግራቸው መዳን የማይችል በመሆኑ ተቆርጧል።

ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረገው የጁዌሪያ ወንድም የሆነው ያሲን መሐመድ ክስተቱን ሲያስረዳ፤ ከውጭ አገር የመጣችውን እህታቸው ከጁዌሪያ ጋር በአየር ማረፊው ከተገናኙ በኋላ እዚያው ፎቶ ሲነሱ በዕለቱ ጠባቂ ከነበረ የፌዴራ ፖሊስ አባል ጋር “ፎቶ መነሳት አይቻለም” በሚል ክርክክር መነሳቱን ይገልጻል።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጁዌሪያ ወንድም ያሲን የእህቱ ግድያ የተፈጸመው “ታቅዶበትና ሆነ ተብሎ በክልሉ መንግስት መሆኑን” እንደሚያምን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። 

“ከአየር ማረፊያው ጠባቂ ፌደራል ፖሊስ ፎቶ አትነሱ በሚል በመካከላቸው ክርክሩ መጋጋሉን ተከትሎ  ጁዌሪያን ግንባሯ ላይ በመተኮስ ህይወቷ እንዲያልፍ አደረገ። በሁኔታው የተደናገጠችውን አህታችንንም ሶስት ግዜ በመደጋገም እግሯ ላይ በጥይት መታት፤ በዚህ ብቻም አላበቃም የ13 አመቱን ታዳጊም እጁ ላይ መታው” ሲል አስረድቷል።

በዚህም ጥቃት የአሜሪካ ዜግት ያላቸው ከውጭ የመጡት አያን አንደኛው እግራቸው ሶስት ግዜ በህክምና እንዲቆረጥ ሆኗል ሲል ያሲን ገልጿል። 

ግድያው ከተፈጸመ በኋላም የጁዌሪያ የግል ኮምፒውተርና ስልክ ተወስዶ ሁሉም ፋይሎች እንዲጠፋ ከተደረገ በኋላ አስረክበውናል ሲል የገለጸው ያሲን ይህም ድርጊቱ “ታቅዶ የተፈጸመ መሆኑን” ያመላክታል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።   

በወቅቱ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ የነበሩት አቶ መሀመድ ጉራይ  ጁዌሪያ መሐመድ በፖሊስ አባሉ “ሆነ ብሎ” በተኮሰው ጥይት መገደላቸዉን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ነገር ግን ግድያው “ፖለቲካዊ” አይደለም ሲሉ ገልጸው፤ “በፖሊሱ እና በፓርላማ አባሏ መካከል በነበረ ክርክር ነው የፖሊስ መኮንኑ በራሱ እርምጃ የወሰደው” ብለዋል።

ወንጀሉ ከተፈጸመ ከወራት በኋላ በክልሉ ምክር ቤት አባል እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በሆኑት ጁዌሪያ የግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ የተመሰረተበት የፀጥታ አባሉ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በሞት ቅጣት እንዲቀጣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፏል

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው በጅግጅጋ ከተማ የጅግጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ሲሆን፤ በፍርድ ሂደቶቹ የሟች ቤተሰቦች እንዳይገኙ መደረጉንና ቅሬታ ማስነሳቱን ያሲን ገልጿል።

የክልል ምክር ቤት አባሏ ጁዌሪያ መሐመድ እና በአደጋው አንድ እግራቸውን ያጡት አያን መሐመድ

“ውሳኔው ተፈጻሚ መደረጉን እርግጠኛ አይደለንም” የሚለው ያሲን፤ “ለክልሉ መንግስት የቅጣት ውሳኔው ተፈጻሚነቱ ከምን እንደደረሰ ጠይቀን፤ ፍቃድ ለሚሰጠው ለኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጥያቄ ቀርቧል ከሚል ምላሽ ውጭ የተነገረን ነገር የለም” ብሏል።

ጁዌሪያ ወንድም ያሲን የእህቱ ግድያ የተፈጸመው “ታቅዶበትና ሆነ ተብሎ በክልሉ መንግስት መሆኑን” እንደሚያምን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። 

የፍትህ ጥያቄና በቤተሰቡ ላይ ተጽዕኖ መድረስ 

ያሲን ፍትህ በመጠየቃችን ማስፈራሪያ፣ ድብደባና እስር በቤተሰቡ ላይ እየደረሰ መሆኑን አስረድቷል። “ጁዌሪያ በተገደሉበት ወቅጥ በሚዲያ ፍትህ በመጠየቄ ለሁለት ወር ለእስር ተዳርጊያለሁ፤ የተፈታሁትም ከዚህ በኋላ ምንም እንዳትናገር ተብየ ማስጠንቃቂያ ተሰጥቶኝ ነው።” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸው ያሲን፤ ከዚያ በኋላም “ዝም እንድንል ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው” ብሏል። 

ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃም ጉሌድ ሱልጣን የተባለ የክልሉ መክር ቤት አባልና የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት የጁዌሪያ መሐመድ የመጀመሪያ ልጅ በመኖሪያ ቤታቸው ፊት በሶስት ፖሊሶች ድብደባ እንደተፈጸመበት እጁ ላይ ጉዳት መድረሱን ያሲን ገልጿል። ድብደባ ከፈጸሙት ከሶስት ፖሊሶች ውስጥ ሁለቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አክሎ ገልጿል።

ያሲን አክሎም የምክር ቤት አባሏ በአየር ማረፊያ ውስጥ በመገደላቸው “አየር መንገዱ ተጠያቂ አልተደረገም እንዲሁም ከሚመለከተው አካል ተገቢው ካሳ አለተሰጠንም” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ያሲን ከዕንባ ጠባቂና ቅሬታ ሰሚ ቢሮ፣ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ልንረዳህ አንችልም” የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድቷል። 

የጁዌሩያ መሐመድ ግድያ እና አያን መሐመድ እግራቸውን ለመቆረጥ ያበቃቸው ወንጀል የተፈጸመው በጅጅጋ አየር ማረፊያ ውስጥ እና በህግ አካል በመሆኑ በአየረ መንገዱ ላይ በዓቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትና ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቋል። 

“የጁዌሩያ መሐመድ ግድያ እና አያን መሐመድ እግሯን ለመቆረጥ ያበቃቸው ወንጀል የተፈጸመው በጅጅጋ አየር ማረፊያ ውስጥ እና በህግ አካል በመሆኑ በአየረ መንገዱ ላይ በዓቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትና ተገቢው ካሳ እንዳልከፈለን ለክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ደብዳቤ እንዲላክልን ብንጠይቅም ፍቃደኛ የሚሆን የህግ አካል አላገኘንም” ብሏል።

በተጨማሪም የጁዌሪያ ገዳይ የተፈረደበት የሞት ፍርድ ተፈጻሚ መሆኑንና ፍትህ መሰጠቱን የክልሉ መንግስት እንዲሳውቅ ጠይቋል። 

የፍትህ ጥያቄ በመጠየቁ ለእስር መዳረጉን፣ ማስፈራርያና ዛቻ በመንግስት አካላት በኩል እየደረሰበት መሆኑን የገለጸው ያሲን በቤተሰቡ ላይ የሚደርሰው ጫና እንዲቆም ተማጽኟል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽንና የፍትህ ቢሮን ኃላፊዎች ለመነጋገር ያደረነው ጥረት ባለመሳካቱ አስታየታቸውን ማካተት አለተቻለም። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button