ዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች በሁለቱ ጎራ ተከፍለው የሚገኙ የህወሓት አመራሮች ግጭቶችን ከሚቀሰቅሱ ተግባራ እንዲቆጠቡ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2016 ዓ.ም፡- በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ ያሉ ሁለቱም ቡድኖች በክልሉ የሚታየውን ፖለቲካ ሁኔታ ወደ ቀውስ የሚከት እና በህዝቡ ዘንድ መከፋፈልን ከሚፈጥሩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስጠነቀቁ።

ሌተናል ጀነራል ታደሰ በተጨማሪም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የተለያዩ አስተዳደር እርከኖች አዳዲስ ሹመቶችን ከመስጠት እና በቦታው የተመደቡ ሰዎችን ከማንሳት ተግባሩ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም በክልሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ተላልፎ የነበረው የድጋፍ ይሁን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን የማድረግ ክልከላ አሁንም በጥብቅ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። ይሄንን ለማስፈጸም ለጸጥታ ሀይሉ ትዕዛዝ ተላልፏል ብለዋል።

ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ትላንት ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ለክልከላዎቹ መነሻ የሆነው ግጭቶች እንዳይፈጠሩ፣በህዝቡ ዘንድ መካፋፈል እንዳይኖር ለማድረግ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

አሁን በክልሉ የተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ከተጋሩ አቅም በላይ ነው ብየ አላስብም ሲሉ የተደመጡት ጀነራሉ አሁን በተጨባጭ እየተጋጋለ ያለው ትኩሰት ግን ከዚህ አቅም በላይ እንዳያደርገው ስጋት አለኝ ብለዋል። አሁን ያለው ግለት መቀጠል ሶስተኛ ወገን እጁን የማስገባት እድሉን እያሰፋ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በክልሉ በማንኛውም ቦታ ስብሰባ ማካሄድ የተፈቀደ ነው ያሉት ጀነራሉ ስብሰባ እንዳይካሄድ ማደናቀፍ ህገወጥ ተግባር ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ስብሰባ እንዳይካሄድ መከልከል ጸረ ህገመንግስታዊ አካሄድ ነው ያሉት ጀነራል ታደሰ ስብሰባ በመከልከል ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም ብለዋል።

ጉባኤ ካሄደው የህወሓት ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩን መቆጣጠር ይፈልጋል፤ በተመሳሳይ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስልጣን የያዘው እና በጉባኤው ያልተሳተፈው የህወሓት ቡድን ደግሞ የወረዳ እና ከተሞቸን አስተዳደሮችን በራሱ ሰዎች መመደብ ይፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል። ይሄ አካሄድ ፖለቲካዊ መፍትሔ ስለማያመጣ ሁሉም ነገር መርገብ አለበት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ አለበት ሲሉ አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ውጥረቱን ለማርገብ ሳይሆን የሚያወሳስቡ ነገሮች እየተበራከቱ በመሆኑ አሁን ያለው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካሄድ እንዲቆም ወስነናል ብለዋል።

ሁሉም ነገር መቆም አለበት እያልን ያለነው ቆም ብለን ማሰብ እንድንችል ነው። ችግሩን የፈጠሩት አካላት ቆም ብለው መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ለማስቻል ነው።

ገዢ የሆነ ህግ ያለው የፖለቲካ ጨዋታ አይደለም እየተከናወነ ያለው፣ የጨዋታ ህግ የለውም፣ ቀይ መስመር የሚባል ነገር የለውም። የህዝቡን አንድነት ጭምር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ነው እየተፈጠረ ያለው።

“አሁን በመካሄድ ላይ ያሉት እንቅስቃሴዎችን ሁሉ እንዲቆሙ እና ችግሮቻቸው በፖለቲካዊ መንገድ እንዲፈቱ” ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ከህወሓት ፖሊት ቢሮ አባላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የጠቆሙት ጀነራል ታደሰ “የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ካልቻሉ ሊያከብሩት የሚገባ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ሥርዓት ሊኖር ይገባል” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ጄኔራል ታደሰ “የፀጥታ ሀይሉ አሁንም ለማንም ሳይወግን ገለልተኛ ሁኖ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፣ በክልሉ ህዝብ ጥቅምና በህዝቡ ደህንነት ላይ ብቻ በማተኮር ይቀጥላል” ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button