ርዕሰ አንቀፅ
በመታየት ላይ ያለ

ርዕሰ አንቀፅ፡ የትጥቅ ግጭት ባለበት፣ ቋሚ ቁርጠኝነት እና የፖለቲካ መፍትሄ በሌለበት ትጥቅ ማስፈታት፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም አያመጣም! ዳግም እንዲታሰብበት ጥሪ እናቀርባለን!

ኢዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/ 2016 ዓ/ም፦  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር የኢትዮጵያን ቀውሶች ወደ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሁኔታ ለማሸጋገር ከብሔራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ጎን ለጎን በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ካደርገባቸው ሶስት የፖሊሲ ምሰሶዎች መካከል የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልና መልሶ የማቋቋም ሂደት (DDR) አንዱ ሆኗል።

በሚያዚያ ወር የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በየአገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ  ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እና በብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚመራው የተሐድሶ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንዳለባቸው አስታውቋል። ምክር ቤቱ “መሣሪያ በማስፈታት፣ የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ በማድረግና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀላቀል፤ ፖለቲካችን ከግንባር ወደ ጠረጴዛ፣ ከጫካ ወደ አዳራሽ እንዲመለስ ማድረግ አለብን” ብሏል። 

“የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልና መልሶ ማቋቋም ውስብስብና እና አስፈላጊ የፖለቲካ ሂደት ነው። ሂደቱ ቀደም ብሎ የግጭቱ መሰረታዊ መንስኤዎችን በሚፈቱ እና ደንብና መመሪያዎችን በሚገልጹ የሰላም ስምምነቶች መደገፍ ይኖርበታል።”

ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ከግጭት በኋላ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል አሳማኝ ማዕቀፍ ሆኖ በሰፊው ተቀባይነያለው ሒደት ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ግን ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮች ጎድለዋል። የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልና መልሶ ማቋቋም ውስብስብና እና አስፈላጊ የፖለቲካ ሂደት ነው። ሂደቱ ቀደም ብሎ የግጭቱ መሰረታዊ መንስኤዎችን በሚፈቱ እና ደንብና መመሪያዎችን በሚገልጹ የሰላም ስምምነቶች መደገፍ ይኖርበታል። እንዲህ አይነት ስምምነቶች ከሌሉ እንዲሁም በመንግስት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል ለሰላም የጋራ ቁርጠኝነት ከሌለ፤ በፖለቲካ ስምምነት የሚሰጡ ማረጋገጫዎች ስለማይኖሩ የታጠቁ ቡድኖች ሒደቱን እንዳይከተሉ ሊያደርግ ይችላል።

ይህ ጉዳይ በተለይ በግጭት በተጎዱ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የታጠቁ ኃይሎችን ትቅጥ ለማስፈታትና መልሶ ለሟቋቋም የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው አካሄድ ውስጥ በግልጽ ይታያል። በኦሮሚያ ክልል ለአምስት አመታት የዘለቀውን የትጥቅ ግጭት ለመቋጨት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና መንግስት መካከል ለሁለት ዙር የተካሄደው ድርድር ፍሬ አላፈራም። ይሁን እንጂ መንግስት “እጃቸውን ሰጥተዋል” ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን ያካተተ፤ ትጥቅ ማስተፋፍና መልሶ ማቋቋም ሲል የሚጠራውን ሒደት ጀምሯል።

በተመሳሳይ መልኩ፤ ፋኖ ታጣቂ ኃይል ከመንግስት ጋር ውጊያ እያደረገ ባለበት አማራ ክልል፤ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ “ተቀብለው የተመለሱና እጅ የሰጡ” በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸውንና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን የክልሉ መንግስት ገልጿል።  ይሁን እንጂ በሁለቱም ክልሎች የታጠቁ ቡድኖች በርካታ አዳዲስ ታጣቂዎችን መመልመላቸውን፣ ማሠልጠናቸውንና ማሰማራታቸውን የቀጠሉ በመሆኑ ተግባሩ የመንግስትን ንግግር ትርጉም አልባ አድርጎታል።

በትግራይ ክልል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና በናይሮቢ የተፈረመው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለመተግበሩ የፌዴራሉ መንግስት ለሁለት አመታት ከተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ወደ ሰላማዊ ስምምነት የመሸጋገር ተግባራዊነት ላይ ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነተ ላይ ጥርጣሬ ጥሏል።  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“የትግበራ ስራው የዘገየው በከፊል በሀብት ማሰባሰብ ውስንነት ምክንያት ሲሆን፤ በዋነኝነት ግን በፌዴራል መንግስት በኩል የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር እና በሁለቱ የስምምነቱ ፈጻሚዎች መካከል ቀጣይነት እና መርህ ያለው ተሳትፎ ባለመኖሩ ነው።”

በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 6 መሰረት፤ ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ በተፈረመ 30 ቀናት ውስጥ ቀላል መሳሪያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የትግራይ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደትን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ በናይሮቢ የተደረሰው የስምምነት የትግበራ ዝርዝር ሰነድ  ፍኖተካርታ አንቀጽ 2.1፤ “ከባድ የጦር መሳሪያ ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት እና የውጭ እና መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ ኃይሎች ከክልሉ ለቀው እንዲወጡ የማድረጉ ስራ በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚከናወን” ይገልጽል። ይህን የመተግበር ኃላፊነት የተሰጠው ለፌዴራል መንግስቱ ነው። 

ነገር ግን የፕሪቶሪያው እና የናይሮቢ ስምምነት ከተፈጸመ 15 ወራት በኋላ፤ በየካቲት ወር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከ270,000 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ የመፍታትና መልሶ የማቋቋም ሂደትን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የትግበራ ስራው የዘገየው በከፊል በሀብት ማሰባሰብ ውስንነት ምክንያት ሲሆን፤ በዋነኝነት ግን በፌዴራል መንግስት በኩል የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር እና በሁለቱ የስምምነቱ ተጻሚዎች መካከል ቀጣይነት እና መርህ ያለው ተሳትፎ ባለመኖሩ ነው።  የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ ሂደቱን አለማጠናቀቁና ግኝቱን ለህዝብ ይፋ አለማድረጉም ሌላኛው ምክንያት ነው።

ይህ የሚያመላክተው በአለምአቀፍ አደራዳሪዎች የሚመቻች እና በሁለት ተፋላሚ ወገኖች ስምምነት የሚከውን ሒደት እንኳ በቁርጠኝነት ካልተደገፈ ለኬታማ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማደራጀት ሂደት ዋስተና ሊሆን እንደማይችል ነው። በትግራይ ውጤታማ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ህብረተሰብ የማዋሃድና መልሶ ማደራጀት ትግበራ ለኢትዮጵያ እንደ ጠቃሚ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። 

“በኢትዮጵያ ትጥቅ የማስተፈታትና መልሶ የማቋቋም ሂደቶችን በገንዘብ ለመደገፍ መሻቱ ያላቸው ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት የትግበራ ሂደቱ በስምምነቱ ደንብና መመሪያ መሰረት መተግበሩን  በእውነተኛ ቁርጠኝነት መከታተል ይኖርባቸዋል።”

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የትጥቅ ግጭት እየተካሄድ ባለበትና በትግራይ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማደረጀት ሂደት ተግባራዊ ባልሆነበት ሁኔታ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና መልሶ የማደራጅ ተግባር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን  ያረጋግጣል በሎ መውሰድ ከሚዲያ ፍጆታ ባለፈ ምንም ጥቅም አይኖረውም።

በድጋሜ ይህ ርዕሰ አንቀፅ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ጥሪ ያቀርባል።  ይህ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማደራጀት ወሳኝ ቅድመ-ሁኔታ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶችና ውንዶችን ህይወት ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዳ በመሆኑ አስፈላጊ ነው። 

በኢትዮጵያ ትጥቅ የማስተፈታትና መልሶ የማቋቋም ሂደቶችን በገንዘብ ለመደገፍ መሻቱ ያላቸው ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ትግራይ ክልልን ጨምሮ የትግበራ ሂደቱ በስምምነቱ ደንብና መመሪያ መሰረት መተግበሩን በእውነተኛ ቁርጠኝነት መከታተል እና ሁሉን አቀፍ መሆኑን እንዲሁም የታለመለትን ግብ መምታቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button