ማህበራዊ ጉዳይጥልቅ ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊነት ለህዳሴ ግድቡ ያለው ፋይዳና ስጋት፤ የግብጽ ቀጣይ እርምጃዎች  

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 18/ 2016 ዓ/ም፦ የናይል ወንዝ ትልቁ ገባር የሆነው የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት አገራት የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀን ስምምነትን ካጸደቁ ከአመታት በኋላ በቅርቡ አንድ ተጨማሪ አገር ተቀላቅላለች፤ ደቡብ ሱዳን። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደቡብ ሱዳን በፓርላማዋ ስምምነቱን ማጽደቋን ተከትሎ “ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው” ሲሉ አሞካሽተውታል።

ተፋሰሱ ሀገራት መካከል ፍትሐዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር ታስቦ እ.አ.አ በ1997 የተቋቋመው የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት፤ በአበይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክቷን በማጠናቀቅ ላይ ላለችው ኢትዮጵያ እንዲሁም ለተፋሰስ አገራቱ የራሱ የሆኑ ጉልህ ሚና ይኖራቸው። 

ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳና ብሩንዲ  ቀደም በለው ስምምነቱን ያጸቁ አገራት ሲሆኑ በቅርቡ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ያጸደቀች ስድስተኛዋ አገር መሆኗን ተከትሎ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽኑ አለም አቀፍ ስምምነት ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።

የናይል ገባር በሆነው አባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሰላ ትችት እና ተቃውሞ ስታሰማ የቆየችው ግብፅ እንዲሁም ሱዳን ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ እራሳቸውን አግለው የቆየች ሲሆን በኋላ ላይ ኢኒሼቲቩን ለመቀላቀል ፍላጎት ቢያሳዩም በአንዳንድ አንቀጾች ላይ ተቃውሞ በማንሳት እስካሁን አልፈረሙም።

የናይል የትብብር ማዕቀፍ እንዲቋቋም ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ውስዳ እንቅስቃሴ ስታደርግ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ በሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት እውቅና የተነፈገው በግብጽ እና ሱዳን መካከል የተደረሰው በ1929 እና 1959 የፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች ናቸው። ግብፅና ሱዳንን በእጅጉ የሚደግፍ እና ሙሉ ለሙሉ እነሱን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ውል በተለይ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ተቃውማዋለች።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በግብጽ እና ሱዳን የተደረሱትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ለመተካት የተቋቋመው የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ ለመሆን ከሚያስፈልገው ከአስራ አንዱ አባል ሀገራት በስድስቱ ሲፀድቅ እና ለአፍሪካ ህብረት ሲቀርብ ነው።

በዚህም መሰረት “የተፋሰሱ ሀገራት የናይል ወንዝን ውኃ በፍትሐዊ መጠቀም ያስችላል፣ ትብብርን ያሳልጣል፣ ስጋት እና ጥርጣሬን ያስወግዳል” በሚል የተዘጋጀው የናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ከ14 አመታት በኋላ የሚፈለገውን የስድስት የተፋሰሱ ሀገራት ፊርማ አግኝቶ ኮሚሽን ለማቋቋም ጫፍ ደርሷል።

ከዚህ በኋላ አፍሪካ ህብረት በ60 ቀናት ውስጥ ናይል ወንዝን የሚያስተዳድር ኮሚሽን እንዲመሰረት በማድረግ  ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ ፍቃድ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። የቀደመው የቀኝግዛት አሳሪ ህግ ለመጨረሻ ግዜ ውድቅ ይሆናል።

የስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምን አስተዋእጾ አለው?

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች ዙሪያ ሱዳንና ግብጽ ጋር ሶስት ዙር ያለ ፍሬ የተጠናቀቁ ንግግሮች ሲያድርጉ ቆይተዋል። 

በሚቀጥለው አመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በተወሰኑ ዩኒቶች ኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሽያጭ መቅረቡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዚህ ሳምንት ገልጿል። በጀት ዓመቱ ከመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል የታላቁ የህዳሴ ግድብ 17 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ነው ተቋሙ የገለጸው። 

ምንም እንኳ ግድቡ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም ኢትዮጵያ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያለው አለመግባባት ለመፍታትና በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ የምታደርገው ድርድር ወደ የትብብር ማዕቀት ስምምነት እንድትወስደው እንደሚያስችላት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።  

“ከፈተኛ ውሃ አመንጪ የሆነ ሀገር የተፋሰሱን አገራት ኑና እንተባበር፣ ተቋም ያስፈልገናል ህግ ያስፈልገናል በሚል የሚለምንበት ሁኔታ/አግባብ የለም፤ ይህ እቤትህ ውስጥ ያለን ዳቦ ጎረቤቶችህን ጠርተህ ይሄን ዳቦ እንዴት እንብላው፣ እንዴት እንካፈለው የማለት ያክል ነው” የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ዶ/ር ጋሻው አይፈራም

በውሃ ተፋሰስ ጉዳዮች ጥናት በማካድ ላይ የሚገኙት የሀይድሮሎጂ ባለሞያው እና የአቪዮኒክ ኢንጂነር አስራት ብርሃኑ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የስምምነቱ ተግባራዊነት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ ገልጸው፤ የወንዙ የበላይ ተጠቃሚ እኔ ብቻ ነኝ የሚል አቋም ስታራምድ ለነበረችው ግብጽ ግን ለመዋጥ የሚያዳግት ሽንፈት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ትብብርን እና የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ የመልማት መብትን አጥብቃ ስታቀነቅን ለነበረችው ኢትዮጵያ ትልቅ ጉልበት ይሰጣታልም ብለዋል። የሀይል ሚዛኑን ተቆጣጥራ ለቆየችው ግብጽ ሚዛኑን እያጣችው ለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

ሃድሮሎጂስት እና የውሃ ሃብት መሃንዲስ ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ በበኩላቸው የኮሚሽኑ መቋቋም የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራትን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን ያለው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። ለዘመናት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ስታቀነቅን ለነበረችው ኢትዮጵያ ምላሽ የሚሰጣት መሆኑን አስታውቀዋል። ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን ለሚጋሩ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን እንቅስቃሴዎችን አድርጋ ምላሽ ያገኘችበት ነው ሲሉ አወድሰዋል።

የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ዶ/ር ጋሻው አይፈራም ግን በዚህ አይስማሙም። ማዕቀፉን በተመለከተ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ክረምት ላይ ለወንዙ ፍሰት ወደ 96 በመቶ የሚያድግ፣ በአጠቃላይ 85 በመቶ ለወንዙ ፍሰት አስተዋጽኦ ያላት ሀገር “ስምምነት ያስፈልገናል ብሎ የሚለምንበት አግባብ በአለምአቀፍ ስትራቴጂ ውስጥ የለም” ሲሉ ተችተዋል።

የአለም ተሞክሮን ካየን፣ ቱርክ እና ቻይናን በአብነት ብታይ የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት ናቸው ትብብር ያስፈልገናል ብለው የሚለምኑት እንጂ ውሃ አመንጪ ሀገር አይለምንም ሲሉ ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ መቋቋም ኢትዮጵያ የተሻለ አማራጭ ፋይናንስ ታገኛለች፣ አጨቃጫቂ አይሆንም የሚል እሳቤ መኖሩን የጠቆሙት ዶ/ር ጋሻው ውሃ አመንጪ የሆነ ሀገር የተፋሰሱን አገራት ኑና እንተባበር፣ ተቋም ያስፈልገናል ህግ ያስፈልገናል በሚል የሚለምንበት ሁኔታ/አግባብ የለም ብለዋል።

“እቤትህ ውስጥ ያለን ዳቦ ጎረቤቶችህን ጠርተህ ይሄን ዳቦ እንዴት እንብላው፣ እንዴት እንካፈለው የማለት ያክል ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ በወንዙ ዙሪያ ያሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮችን አሁንም የማስቀረት እድሉ ጠባብ መሆኑን ያብራሩት ዶ/ር ጋሻው ለአብነትም በትብብር ማዕቀፉ ውስጥ ሁለት የተለያዩ የሚጣረሱ ምርህዎችን አንድ ላይ ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

አንደኛው ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም (equitable and reasonable utilization) ነው ሲሉ ገልጸው ሁለተኛው ጉልህ ጉዳትን ማስቀረት (not to cause significant harm) የሚለው መሆኑን አስታውቀዋል።

ጉልህ ጉዳትን ማስቀረት የሚለው የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት በማይጎዳ መልኩ ማለት ነው፤ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ደግሞ የላይኞቹ የተፋሰሱን ሀገራት ፍላጎት የሚጠብቅ ነው ሲሉ ገልጸው ሁለቱ በጣም ተጻራሪ የሆኑ ህጎችን ነው አንድ ላይ ያስቀመጠው ብለዋል።

ይህንንም ያመጡት ከመንግስታቱ ድርጅት ለማጓጓዣ የማይውሉ ውሃዎች አጠቃቀም ስምምነት ነው ሲሉ ገልጸው ይሄንን ኮንቬንሽን ኢትዮጵያም ግብጽም አላጸደቁትም፤ እነ ቱርክ፣ ቻይና እና መሰል የአለማችን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራተ ተብለው የሚጠሩ ሀገራት የመልማት አቅማችንን ይገድባል በሚል ውድቅ ያደረጉት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የትብብር ማዕቀፉ ላይ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ ግምት ውስጥ የሚገቡ ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል ኢትዮጵያን በተሻለ ሁኔታ ሊጠቅም የሚችለው አንድ ነጥብ አለ ሲሉ ጠቁመው ይህም ሀገራቱ ለወንዙ ውሃ ያላቸው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ይገባል የሚል መካተቱን አስታውቀዋል።

አሉታዊ ነጥብ ብለው የጠቀሱት የሃይድሮሎጂ ባለሙያው ዶ/ር ጋሻው አሁን እየተጠቀሙት ያለውን የውሃ መጠን ግምት ውስጥ እንዲገባ ሊደረግ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

“ከታሪክ አንጻር፣ የቀኝ ግዛት አሻራን እስከመጨረሻው ከማስቀረት አንጻር፣ ኢፍትሃዊነትን ከማስቀረት አንጻር ስታየው፣ ግብጽ የምትከራከርበት ነጥቦች ከማስቀረት አንጻር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አወንታዊ ጥቅሙን አብራርተዋል።”

የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና ለቀጣይ ጉዳዮች የሚኖረው ሚና

የሀይድሮሎጂ ባለሞያው እና የአቪዮኒክ ኢንጂነር አስራት ብርሃኑ አምና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተከናወነው የውሃ ሙሌት በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ያስከተለው ጉዳት አለመኖሩን አስታውሰቅ ለዚህም እ.አ.አ ጥር 17 ቀን 2023 ዓ.ም የግብጹ የመስኖ ሚኒስትር በሀገሪቱ ምክር ቤት ተገኝተው የውሃ ሙሌቱ ያስከተለው ጉዳት የለም ሲሉ መናገራቸውን በአብነት አስቀምጠዋል። በዚህ አመት ውሃ ሙሌት በይፋ ባይካሄድም ግድቡ ውሃ መያዝ ምንም አይነት ውጥረት እንደማይፈጥር በአጽንኦት ገልጸዋል።

የግብጹ አስዋን ሀይ ግድበ በቂ ውሃ መያዙም ሌላኛው አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል።

“ግብጽ በቀጣው ከሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ጋር የፈጸመችውን ወታደራዊ ስምምነት ጠቅሰወ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከራ አይቀሬ ነው” የሀይድሮሎጂ ባለሞያ እና የአቪዮኒክ ኢንጂነር አስራት ብርሃኑ

የውሃ ሙሌቱ እየተጠናቀቀ በሄደ ቁጥር ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚኖረው ተጽእኖ ግልጽ እየሆነ ይመጣል ሲሉ የገለጹልን የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ዶ/ር ጋሻው አይፈራም ግልጽ እየሆነ በመጣ ቁጥር በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው ጫና እየቀነሰ ነው የሚሄደው፤ መደበኛ የሆነ የውሃ ፍሰት ነው የሚኖረው ይሄንን አለምአቀፉ ማህበረሰብም የሚያየው ይሆናል ብለዋል።

ችግር የሚሆነው የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በተለይ ደግሞ ግብጾቹ በሚያቀርቧቸው ተያያዥ ጉዳዮች አማካኝነት መሆኑን የጠቆሙት ጋሻው ለመስኖ የሚጠቀምበትን ለም አፈር በማስቀረት ተያያዥ ጥቅሞች እናጣለን ማለታቸው አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል።

ሙሌቱ እያለቀ በመጣ ቁጥር ብዙ ጉዳዮች ወይንም ካረዶች እየተጣሉ፣ አጨቃጫቂነቱ እየቀነሰ ነው የሚመጣው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

የውሃ ሙሌቱ መቀጠል አወንታዊ ተጽእኖ በሚል ስንከራከርባቸው የቆዩ የጎርፍ መቀነስ፣ ጎርፍ ሲቀንስ መስኖ መጨመሩ፣ በጎርፍ የሚደርስባቸው የሰው እና ማህበራዊ አደጋም መቅረቱ፣ የሃይድሮ ግድቦቻቸው የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም መጨመር እየጎሉ ይሄዳሉ ሲሉ እምነታቸውን አስቀምጠዋል።

ቀጣዩ የግብጽ መንገድ ምን ሊሆን ይችላል?

ግበጽ የ1959 የቀኝ ግዛት ውል የሰጣትን በወንዙ በበላይነት ተጠቃሚ የመሆን እድልን ለማስቀጠል በዋናነት ኢትዮጵያ ላየ ያተኮረ ቀጣይ ካርዶች መምዘዟ የማይቀር ነው ሲሉ ምልከታቸውን ያጋሩን አስራት በተለይም ከኢትዮጵያ አጎራባች ሀገራት ጋር ወታደራዊ ትብብር እና የመረጃ ልውውጥ በመፈራረም ከበባ ማካሄዷ የማይቀር ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ለአብነትም ግብጽ ከሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ጋር የፈጸመችውን ወታደራዊ ስምምነት ጠቅሰወ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከራ እንደማይቀር ገልጸዋል።

በተጨማሪም “ጦሯን የምታሰፍርበት የጦር ሰፈር ከሀገራቱ በመውሰድ ማቋቋሟ የማይቀር ነው፤ በጦር ዞን እንዲኖራት ታደርጋለች፤ ከሱዳን፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ ጋር እያደረገች ያለውም ይህንኑ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ በመነጠል ድጋፍ እንዳታገኝ የማድረግ ስትራቴጂ መከተሏ አይቀርም ሲሉ የገለጹት አስራት “የስለላ መረጃዎችን የምታገኝበትን እድል እያሰፋች ኢትዮጵያ ግን እንዳታገኝ የማድረግ እንቅስቃሴዋ ሰፊ ይሆናል” ብለዋል።  

“የሚዲያ እና ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ” አንደኛው የግብጽ የመጫወቻ ካርድ መሆኑን የጠቆሙን አስራት የህዝቡን አመለካከት የመቅረጽ ስራ መስራቷ አይቀርም ብለዋል። አለም አቀፉ ማህበረሰብ በግብጽ የሚፈጠሩ አወንታዊ ሁኔታዎችን በግድቡ ተጽእኖ ሳቢያ የተፈጠሩ የሚያስመስል ምስል እንዲኖረው በማድረግ ድጋፍ ለማግኘት መጣሯ የማይቀር ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ዶ/ር ጋሻው አይፈራም በበኩላቸው ለግብጾቹ አመቺ የሆኑ ቀጠናቂ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁመው የሱዳን መተራመስ፣ የኢትዮጵያ እና ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት የተፈጠረው ውዝግብ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።

በዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ከሌሎቹ ጎረቤቶቿ የተነጠለች እንድትሆን ማድረግ ሌላው ካርዷ ይሆናል ሲሉ ግምታቸውን የነገሩን ጋሻው በአብነትም ከሲያድባሬ ጀምሮ ሶማሊያን በመደገፍ ኢትዮጵያን ማዳከም የሚለው ቀድሞ ጨዋታቸውን ጀምረዋል ሲሉ አንስተዋል።

ግብጽ ማለት በቅርብ ርቀት ላይ ያለች፣ ከጎረቤቶቻችን የምትልቅ ጎረቤት አገር ናት ያሉት ጋሻው “ከበባ መፈጸም የምትጠቀመው ቀጣይ ካርዷ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

እድሉን ካገኙ “የእጅ አዙር ጦርነት ለማካሄድ መሞከራቸው አይቀርም” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸው፤ “ሰርጎ ገቦችን በማገዝ ጥቃቶችን መፈጸም መሞከራቸው አይቀሬ መሆኑን” አስታውቀዋል።

ይህም ያለመረጋጋት የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው፣ በውሃ ልማት ላይ ሊውል የሚችል ሀብት በማዛባት፣ ኢትዮጵያ ልታካሂደው የምትችለውን የውሃ ሀብት ልማት ይልቅ ወደ ጦርነት ሀብቶቿን በማፍሰስ ፍላጎታቸው እንዲሳካ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።

የትብብር ማዕቀፉን ያልፈረሙ ሀገራት ቀጣይ እንቅስቃሴ እና አቋም ዙሪያ ምን እንጠብቅ

የስምምነቱን ማዕቀፍ በምክር ቤት ደረጃ ያላጸደቁት እነ ሱዳን እና ኬንያ እንዲሁም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋነኛ ምክንያታቸው አሰላለፉን በጥንቃቄ በመመልከት የተሻለ እድል/ጥቅም ለማግኘት በሚል ነው የሚል እምነት አለኝ ያሉን አስራት በተለይ ሱዳን ለበርካታ አመታት የግብጽ አጋር ሁና መቆየቷ እንደሌሎቹ ሀገራት ፈጥኖ ማጽደቁ ከባድ እንደሚሆንባት እሙን ነው ሲሊ ገልጸዋል።

ነገር ግን ይላሉ አስራት በቀደመው የቅኝ ግዛት ውል ተጠቃሚነቷ ውስን ስለሆነ እና የህዝብ ቁጥሯን የሚመጥን ተጠቃሚነት ስለምትሻ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ፍትሐዊ ክፍፍል ለማድረግ መወሰኗ አይቀሬ ነው ሲሉ ሞግተዋል።

ኬንያ የትብብረ ማዕቀፉን መፈረሟን ያወሱት አስራት በፍትሀዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ አቋሟ ከላይኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር አንድ በመሆኑ የማስጸደቋ ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ዶ/ር ጥሩሰው በበኩላቸው ግዜ ይፈተዋል ሲሉ ገልጸው የትብብር ማዕቀፉን ፈርማ ያላጸደቀችው ኬንያ መሆኗን አውስተዋል። 

የትብብር ማዕቀፉ ቢዘገይ እንኳ ግብጽን እንጂ ኢትዮጵያን የበለጠ አይጎዳም ሲሉ የሚሞግቱት አስራት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ሉዐላዊነታቸውን በሚያስከብር መልኩ ፍትሀዊ የሆነ ድርሻ እንዲጠይቁ ይበልጥ በመገፋፋት ላይ ናቸው ብለዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button