ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች እንዳሳሰበው ገልጸ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 18/ 2016 ዓ/ም፦ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ወቅታዊ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ባለው ጥረት እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች እንዳሳሰበው ገልጿል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ እነዚህ ተግዳሮቶች እየተባባሱ የመጡት፤ በመካሄድ ላይ ያሉ ግጭቶች በመቀተላቸው፣ የዋጋ ግሽበት እና ለሰብአዊ ድጋት ጥረቶች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው ነው ብሏል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በነሐሴ 23፣ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያን አስከፊ የምግብ አቅርቦት ችግር አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፤ ከሐምሌ እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እርዳታ ካልጨመረ ሁኔታው ​​ሊባባስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በዚህ ወሳኝ ወቅትም የሚሰጠው ድጋፍ ካልተጠናከረ የከፋ ውጤት ሊመጣ የሚችልበት ዕድል እንዳለ አጽንኦት ሰጥቷል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም በተለይ እተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ በመላው ኢትዮጵያ 15.8 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

ድርጅቱ በተለይ እንደ አማራ እና ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ፣ የሰራተኞችን ደህንነት አደጋ ላይ እየጣለ እና በአሰራር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጿል።

አዲስ ስታንዳርድ ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኛ በሆነው ያሬድ መለሰ ላይ የተፈጸመውን ግድያ መዘገቡ ይታወሳል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የረድኤት ሰራተኛው የያሬድ መለሰ ሞት በዚህ አመት በኢትዮጵያ የተገደሉትን የረድኤት ሰራተኞች ቁጥር ወደ ስምንት ያደረሰ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ስድስቱ የሞቱት በአማራ ክልል ነው።

የአለም የምግብ ፕሮግራም በቅርቡ ባወጣው የምግብ እና የተመጣጠነ የአመጋገብ ዋስትና መረጃው እንደገለጸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት የብር ዋጋ ማሽቆልቆሉ በድህነት ውስጥ ባሉ ቤተሰቦች ላይ አፋጣኝ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ያደረገው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለብር ዋጋ መቀነስ ምክንያት መሆኑን ገልፆ ይህም ለምግብ ዋጋ መናር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እና በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ለምግብ ዋስትና እጦት እንደሚዳርጋቸው ትንበያውን አስቀምጧል።

በቅርቡ መንግስት ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በሀገሪቱ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ በተለያዩ የፍጆታ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየ ሲሆን፤ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና ምርትን ባከማቹ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን መዘገባችን ይታወሳል

የአለም የምግብ ፕሮግራም ከጸጥታ ችግር እና የምግብ ዋጋ ንረት ተግዳሮቶች ባሻገር የበጀት ክፍተት መኖሩ ስራውን እያስተጓጎለው እንደሚገኝ እና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የመድረስ አቅምን እየገደበ መሆኑን ጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ላሉ ከ10.9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ የሚውል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 278 ሚሊዮን ዶላር እና በሚቀጥሉት አስራ ሁለት ወራት ደግሞ 776 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

ነገር ግን አዲስ የገንዘብ ድጋፍ እስካልተገኘ ድረስ 55 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የምግብ እርዳታ ያገኛሉ ብሏል።

ቅድሚያ ከተሰጣቸው 10.9 ሚሊዮን በላይ የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ካጋጠማቸው ሰዎች በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ታስተናግዳለች።

የአለም የምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው፤ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በመኖሩ በቂ የገንዘብ ድጋፍ እስኪገኝ ድረስ አዲስ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ መጤዎችን ሳይጨምር በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞች ከምግቡ 60 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ማግኘታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጿል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button