ዜናቢዝነስ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ሀብቱ 672 ቢሊየን ብር ቢደርስም 367 ቢሊየን ብሩ በዕዳ የተመዘገበ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7/2016 ዓ.ም፡-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ በሚያካሂደው የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ማሻሻያ ዙሪያ ከተቋማት እና ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እየመከረ መሆኑን አስታውቋል።

ትላንት ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ከተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማካሄዱን እና በዛሬው ዕለትም የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞቹ ጋር በመምከር ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቅርቡ የሚያደርገው የታሪፍ ማሻሻያ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ሲሉ የሁለቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች በምክክር መድረኩ ላይ ተናግረዋል።

የታቀደው የታሪፍ ክለሳ የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግ እና አገልግሎቱን ለማሻሻል  ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ሀብቱ 672 ቢሊየን ብር ቢደርስም 367 ቢሊየን ብሩ በዕዳ የተመዘገበ ነው ሲሉ የተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ ከሚዲያ ሃላፊዎች ጋር ባካሄዱት ምክክር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከውሃ 4 ሺህ 820 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 404 ሜጋ ዋት እና ከእንፋሎት 32 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨች ትገኛለች ብለዋል።

የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ከ20 ሺህ 200 በላይ ኪሎ ሜትር መድረሱን የጠቀሱት አቶ አንዱዓለም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ 3ኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት የምታስተዳድር ሀገር ናት ሲሉም ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ተቋሙ በ2021 ዓ.ም የግል ባለሃብቱን በማሳተፍ የኃይል ማመንጨት አቅምን ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያብራሩት ሥራ አስፈፃሚው ከውሃ 6 ሺህ 166 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 2 ሺህ 255 ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት 1 ሺህ 500 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከፀሐይ 975 ሜጋዋት ተጨማሪ ኃይል ለማግኘት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ በ2023 ዓ.ም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ወደ 30 ሺህ 345 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ብዛት ወደ 323 ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

ተቋሙ ለኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ200 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ከ25 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል ሲሉ ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።

ተቋሙ እየተስተዋሉ የሚገኙ የኃይል መቆራረጦችን ለመቅረፍም የመሰረተ ልማት ማዘመን፣ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ፣ የውስጥ አቅምን እና የፋይናንስ ቁመናን የማሳደግ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የጠቆሙት።

የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የኢነርጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሰኢድ እንደገለፁት የታሪፍ ማሻሻያው በየአራት ዓመቱ መከለስ የሚገባው ቢሆንም ሳይሻሻል በመቆየቱ በኃይል አቅራቢ ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

በባለሥልጣኑ በመመሪያ ቁጥር 008/2014 መሠረት የታሪፍ ክለሳ ሲደረግ ኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የኦፕሬሽን ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ የሚያደርግ ታሪፍ መዘጋጀት እንዳለበት እንደሚደነግግም ተናግረዋል።

የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በፋይናንስ እና በአሰራር ጠንካራ ሆነው የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲችሉ የታሪፍ ክለሳው ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ነው አቶ አህመድ የገለፁት። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button