ዜናፖለቲካ

ዜና: የግብጽ ጦር በሶማሊያ መስፈር በጽኑ አወግዛለሁ ስትል ሶማሊላንድ ገለጸች፣ ቀጠናውን ካለማረጋጋት ባለፈ አስጊ ነው ብላለች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24/2016 ዓ.ም፡- የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና አለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የግብፅ ጦር በሶማሊያ መስፈሩን አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታወቀ።

የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰፍር መደረጉ ያለ በቂ ምዘና እና ግምገማ የተከናወነ ነው ሲል የጠቀሞው መግለጫው ለሶማሊያ እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አለመረጋጋት ምክንያት ከመሆን ያለፈ አስጊ ነው ሲል ገልጿል።

“የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰፍር መደረጉ በሶማሊላንድ እና በቀጠናው በሚገኙ ሀገራት የአመታት ጥረት በቀጠናው የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም የሚያውክ ሁኖ አግኝተነዋል” ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው አትቷል።

በምንም ምክንያት ይሁን “የውጭ ወታደራዊ ሃይል ወደ ጎረቤት ሶማሊያ መግባቱ ቀጣናውን ወደ አለመረጋጋት የሚወስድ፣ በቀጠናው በመካሄድ ላይ ያለው የሰላም ጥረት የሚያዳክም፣ አስከፊ መዘዝ ይዞ ሊመጣ የሚችል ውጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው” ብሏል።

“በአፍሪካ ቀንድ እንደሚገኙ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ሁሉ ሶማሊላንድ የህዝባቿን መረጋጋት እና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም የሌላ ሀገር ወታደራዊ ሀይል መስፈርን አንቀበልም” ሲል ገልጿል፤ “አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን አደገኛ የግብፅ እርምጃ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን” ብሏል።

“የሶማሌላንድ በከፍተኛ ጥረት ያገኘችውን ሰላሟን እንዲሁም የአካባቢውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት ሲፈጸሙ እያየች ዝም አትልም ሲል” አስጠንቅቋል።

“አለም አቀፍ አጋሮቻችን ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ በቅርበት እንዲከታተሉት” ሲል የጠየቀው መግለጫው “የሶማሌላንድ እና የቀጠናወን ደህንነት እና መረጋጋት ለመጠበቅ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስዱ” ሲል አሳስቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ማምሻውን “በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ” ዙሪያ በሰጠው መግለጫ “የሶማሊያ መንግስት ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል መተቸቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ “በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል” ያለው መግለጫው “ቀጠናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል” ሲል ማስታወቁ በዘገባው ተካቷል።

ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየቷን እና ነሃሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ወታደሮች እና መሳሪያዎች የጫኑ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተያዘው ወር መጀመሪያ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ወደ ካይሮ በማቅናት ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር መገናኘታቸውን እና ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button