ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ግብጽ በተደጋጋሚ የምታቀርባቸው ዛቻዎች እና አቤቱታዎች “መሠረተ-ቢሶች” ናቸው ስትል እንደማትቀበለው ኢትዮጵያ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ ግብጽ በተደጋጋሚ የምታቀርባቸው ዛቻዎች እና አቤቱታዎች “መሠረተ-ቢሶች” ናቸው ስትል እንደማትቀበለው ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ አስታወቀች፤ የመንግስታቱ ድርጅትን ቻርተር በሚጻረር መልኩ እየሰነዘረችብኝ ያለችውን ተደጋጋሚ ዛቻ ምክር ቤቱ እንዲያጤንልኝ ስትል አሳስባለች።

ኢትዮጵያ ይህን የገለጸችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ነው።

አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ እንደሚያሳየው “ኢትዮጵያ በፍትሐዊ የናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ያላትን ቁርጠኝነት ገልፆ ግብጽ የአባይ ውሃን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን” ኮንኗል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤት የላከው ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አምስተኛ ዙር የዉሃ ሙሌት ማከናወኗን ተከትሎ ግብጽ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጽጥታው ምክር ቤት የጻፈችውን ደብዳቤ ተከትሎ ነው፤ ግብጽ በደብዳቤዋ የግድቡን ውሃ አሞላል “የአንድ ወገን ፖሊሲ” በማለት እንደማትቀበለው አስታውቃለች።

በግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባዳረ አብዱላቲ የተፈረመው ደብዳቤ: “የኢትዮጵያ አካሄድ የአለም አቀፍ ህግ መርህዎችን እና በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የፈደረሰውን የመርሆች ስምምነትን የሚጥስ ነው” ሲል መቃወሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ስላሴ ለጸጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ “ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ያቀረበችውን መሠረተ-ቢስ ክስ ሙሉ በሙሉ አንቀበለውም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት በላከችው በዚህ ደብዳቤ በቅርቡ የግብጹ ጠቅላይ ሚንስትር “በየትኛውም አገር የሚከናወን የልማት ፕሮጀክት: ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ በማይቀንስ ሁኔታ መካሄድ አለበት” ሲሉ መናገራቸው ጠቅሳ “ግብፅ አሁንም በቅኝ-ግዛት ህጎች እና አስተሳሰቦች በመመርኮዝ  በአባይ ውሃ ላይ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን ያንጸባረቀ ነው” ስትል ኮንናለች።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪ ደብዳቤው ግብጽ “አዋጭነታቸው ያልተረጋገጡ” የልማት ፕሮጀክቶችን የወንዙን ተፋሰስ ሀገራት ሳታሳውቅ ስትገነባ መቆየቷን ኢትዮጵያ ስታሳውቅ እንደነበረ አስታውሶ: ይህም የሌሎቹን የተፋሰስ ሃገራት ጥቅም እና ፍላጎት ያገለለ መሆኑን አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ባቀኑ ወቅት ከፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ጋር የግድቡን ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን በተመለከተ የሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲደረግ ከስምምነት ደርሰው እንደነበር የገለጸው ደብዳቤው ይሁን እንጂ ግብጽ የሶስትዮሽ ድርድሩን ጥላ መውጣቷን አስታውሷል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ በዚህ ደብዳቤ ላይ እንደገለጸችው የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና ሱዳን ሀገራት የሶትዮሽ የባለሙያዎች ቡድን ባስቀመጠው እና በተስማሙት መርህ መሰረት የግድቡን ውሃ ሙሌት እያከናወነች መሆኗን ገልጻለች።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ወይም በአጠቃላይ የትብብር ሕግ ማዕቀፍ ስር ሆና ሁሉን ሊያግባባ የሚችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ትገኛለች ሲሉ ገልጸዋል።

ሆኖም ግብፅ በሰላማዊ መንገድ ከመደራደር ይልቅ ለጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ የምትልካቸው ዛቻ እና አቤቱታዎች ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት ፈጥሯል ብሏል።

ደብዳቤው አክሎም ግብፅ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር በሚጻረር መልኩ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰች ያለችውን ተደጋጋሚ ዛቻ ምክር ቤቱ እንዲያጤን አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button