ቢዝነስጥልቅ ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ የኢትዮጵያ ውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው አሉታዊ ወይንስ አዎንታዊ ለውጥ?

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ8/2016 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሆነ በሰፊው እየተስተዋለ ይገኛል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብር ዋጋ ማዳከምን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ለውጥ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጹ ትንበያዎች በብዙዎች ዘንድ በስፋት ሲነገሩ ሰንብተዋል::

ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መግለጫ፤ ጉዳዩን በትክክል አብራርቷል:: መግለጫው ኢትዮጵያ ከቋሚ የምንዛሬ ተመን ስርዓት ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት እየተሸጋገረች መሆኑን ይገልጻል::

በገበያ ላይ የተመረኮዘ የምንዛሬ ተመን በመባል የሚታወቀው የውጭ ምንዛሬ አሰራር የአንድ ሀገር ገንዘብ ዋጋ ከሌሎች ምንዛሬዎች አንፃር በአቅርቦትና በፍላጎት የሚወሰንበት ነው::

ኢትዮጵያ መንግስታት ሲለዋወጡ የተለያዩ የምንዛሬ ተመን ስርዓቶችን ስትከተል ቆይታለች። ከ1976 እስከ 1992 (እ.ኤ.አ) ባለው ጊዜ ውስጥ  አንድ የአሜሪካን ዶላር 2.07 የኢትዮጵያ ብር ነበር::ይህ ቋሚ የምንዛሪ ተመን ለሁለት አስርት ዓመታት ሳይቀየር የቆየ ሲሆን በዚህም ምክንያት የብር ዋጋ ከአሜሪካ ዶላር እና ከሌሎች በርካታ የውጭ ምንዛሬዎች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው አስችሎት ነበር::

በ1992 የተደረገውን የገንዘብ ዋጋ መቀነስን ተከትሎ፣ የምንዛሪ ሥርዓቱ በቋሚ ተመን ከሚመራ ወደ መንግሥት የሚያስተዳድረው ተንሳፋፊ የምንዛሬ ስርዓት ተለወጠ።

ይህም የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት እስካለፈው ሳምንት ድረስ ማለትም ብሔራዊ ባንክ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መቀየሩን እስከገለጠበት ጊዜ ብስራ ላይ ቆይቷል::

የውጭ ምንዛሪ ስርዓት ማሻሻያውን ተከትሎ የብር ዋጋ የመግዛት አቅም ከዋና ዋና አለም አቀፍ የገንዘብ አይነቶች አንፃር 40 በመቶ ያህል ተዳክሟል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በያዝነው ሳምንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ የአሜሪካን ዶላር 103. 96 የኢትዮጵያ ብር መድረሱን አስታውቋል።

የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ትግበራው አዲስ መመሪያን ያካተተ ሲሆን ይህም አሁን በሥራ ላይ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንደሚቋቋሙ ተገልጿል:: ለእነዚህ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሸጡ የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጣቸውም ተጠቁሟል።

ፈተና ወይስ አዎንታዊ ለውጥ?

ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የተካሄደው ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለምረጋጋትና መዛባትን ያስተካክላል ሲል ገልጿል። 

ባንኩ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ቀደም ሲል ተግባራዊ ሲደረግ የሰነበተው የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፣ መጀመሪያ ላይ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለማረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ለመግታት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ባልታሰበ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ትይዩ የገበያ ዋጋ እንዲፈጠርና የዋጋ ንረት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጿል::

መግለጫው “ነባሩ አሰራር የኢትዮጵያን ውድ ሀብቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ከመደበኛው የባንክ አሰራር እና ከሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ውጪ ያደረገ ነው” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

መግለጫው አያይዞም እንዲህ ያሉ ተግባራት በኢትዮጵያ ምርታማ ዘርፎች ላይ የተወሰኑ ህገወጥ ቡድኖች እና በመካከላቸው የሚገኙ ደላሎችን አላግባብ ተጠቅሚ ያደረገ ሲሆን በአንጻሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል::

ወደ ገበያ-መር የምንዛሬ ተመን አወሳሰን በመሸጋገር በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማግኘት እንደሚቻል ብሔራዊ ባንክ ይገልጻል::

እንደ ብሔራዊ ባንክ ገለጻ፣ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የወጭ ምንዛሬ አቅም በማሳደግ ለዜጎቿ እንዲሁም ለአምራች የኢኮኖሚ ሴክተሮች ተጠቃሚነት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱን ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠናክር ሲሆን ይህም ልዩ ልዩ ስራዎችን ለማስፋት እና ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስችላል ተብሏል::

ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት፤ የምንዛሬ ዋጋ የሚወሰነው ገበያ ውስጥ ባለው የአቅርቦት እና የፍላጎት መጠን ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገራት በርካታ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ጥናቆች ያመላክታሉ።

እነዚህ ጥቅማ ጥቅሞች ተለዋዋጭነትን፣ የተሻለ የሀብት አሰባሰብንና ተወዳዳሪነትን፣ የኢንቨስትመንት እድገትን እና የውጭ ምንዛሬ ክምችት ፍላጎት መቀነስን ያጠቃልላል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደዚህ ያሉ እርምጃዎች በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ላይ የኢኮኖሚ መረጋጋትን እና እድገትን የሚጎዳ ነው ሲሉ ይሞግታሉ::

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ እና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ቢሮ ውስጥ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሄኖክ ፋሲል ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ እንደሆነ ይገልጻሉ።

አክለውም ደካማ ተቋማዊ አሰራር፣ የቁጥጥር ማነስ፣ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እጥረት፣ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እና ዝቅተኛ የሆነ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ላለበት አስተዳደር  ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ነው ሲሉ ያስረዳሉ::

“በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ያለን ኢኮኖሚ ለሚመሩ ሃገራት በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ሊያደርጋቸው ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል::

እንደ ሄኖክ ፋሲል (ዶ/ር) ገለጻ፣ በገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ውስጥ ያለው ተለዋዋጭነት ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትን የሚያባብስ ሲሆን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር፣ የምንዛሬ ተመንን ለማረጋጋት እና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት እንቅፋት ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል::

ከዚህም በላይ እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት ወይም የሸቀጦች ዋጋ መዋዠቅ ያሉ ውጫዊ ተግዳሮቶች በኢኮኖሚው ላይ የበለጠ ጉልህ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ አክለዋል::

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ገበያ መር የምንዛሬ ተመን ሥርዓት መከተልን በተመለከተ ስጋታቸውን ከገለጹ ባለሙያዎች መካከል ሌላኛው አንጋፋ የምጣኔ ሀብት ሊቅ የሆኑት ክቡር ገና ይገኙበታል::

አቶ ክቡር ገና ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ መንግሥት ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመጨረሻ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ሲሉ ይገልጻሉ:: ሊኖሩ የሚችሉ ጥቅሞች ማለትም እንደ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መስፋፋት፣ ብድር፣ የገበያ ዕድገት እና የኢንዱስትሪ ድጋፍ ዕድገቶች በረጅም ጊዜ ውስጥ ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል:: 

አክለውም” እነዚህ ጥቅሞች ሊገኙ የሚችሉት ወሳኝ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ነው” ሲሉ አበክረዋል::

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሬ ተመን ሥርዓት ከመተግበሩ በፊት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና አንዳንድ ፖሊሲዎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ:: አክለውም በ1970ዎቹ ውስጥ ቻይና ከተጠቀመችው ስትራቴጂ ጋር በንጽጽር ሲታይ ሀገሪቱ በወቅቱ ሆን ብላ ገንዘቧን የመግዛት አቅም በማዳከም በዓለም ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት አሳድጋ የነበረችው ባላት ጠንካራ የማምረት አቅም ተደግፋ ነበር ሲሉ አስረድተዋል::

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ባላት ደካማ የኢንዱስትሪ እድገት እና አነስተኛ የግብርና ምርት የተነሳ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ተግዳሮት ሊያጋጥማት ይችላል ሲሉ አብራርተዋል::

አክለውም “ኢትዮጵያ የማምረት አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ ካላሳደገች እና እየተከሰቱ ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ካልፈታች በስተቀር በቅርቡ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የመግዛት አቅምን ሊቀንስ እና ድህነትን ሊያባብስ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በቅርቡ የተካሄደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በረጅም ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስን ለማስተካከል ሆን ተብሎ ከመንግስት ተነሳሽነት የመነጨ እንዳልሆነ ጥርጣሬኣቸውን ይገልጻሉ። በአንጻሩ አዲሱ ፖሊሲ ባጋጠመ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ይፋዊ በሆነው እና ትይዩ በሆነው ጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ መካከል ባለው ከፍተኛ ልዩነት ምክንያት የተከሰተ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። 

በተጨማሪ ኢትዮጵያ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን የተቀበለችው እንደ አይ.ኤም.ኤፍ. ባሉ የብሬትተን ውድስ ተቋማት ባሉ ጫናዎች ተገድዳ እንደሆነ ይህም  ከአበዳሪ ተቋማቱ ብድር ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን በማንሳት ይሞግታሉ::

ዶ/ር ሄኖክ ይህን ሃሳብ ከሚደግፉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው:: “እንዲህ ያለው የውጭ ጫና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን በመሸርሸር አገሪቱ ከረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ልማት ይልቅ የአጭር ጊዜ የፋይናንስ መረጋጋትን እንድታስቀድም ያስገድዳታል” ሲሉ ይገልጻሉ::

ሊፈጠሩ ከሚችሉት ችግሮች መካከልም ለውጭ ዕርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ መሆን፣ ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ተጋላጭነት መጨመር እና በሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ጭና  የሚፈጥረው ማኅበራዊ አለመረጋጋት ይገኙበታል።

ሌላኛው በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ መርድ ቱሉ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ለመሸጋገር ያሳለፈው ውሳኔ እነዚህ የብድር ተቋማት በተለይም ከብድር ስምምነቶች እና ከኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ባሳደሩት ተጽዕኖ የተደረገ ነው ይላሉ።

“ማሻሻያው የዕዳ ክፍያን እና ካፒታልን በኢኮኖሚ ውስጥ ማስገባትን ይጨምራል። ይሁን እንጂ የእነዚህ እርምጃዎች ስኬት የሚወሰነው መንግስት የሚመነጨውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር ከቻለ እና የሚኖሩ ጥቅሞችን በኢኮኖሚው ውስጥ በስፋት መሰራጨታቸውን ማረጋገጥ ከተቻለ ነው” ሲሉ ባለሙያው ይገልጻሉ።

በቅርቡ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ. የእርዳታ ገንዘብ ለማግኘት በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጪ ምንዛሬ ስርዓትን የተከተሉ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ልምድ የታሰበውን ያህል ውጤት አላመጣም።

እ.ኤ.አ በግንቦት 2023 ናይጄሪያ ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ተሸጋግራ የነበረ ሲሆን የናይጄሪያ መንግስት ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እና የሀገር ውስጥ ምንዛሬን ለማረጋጋት ተስፋ አድርጎም ነበር::

ይሁን እንጂ የናይጄሪያ መገበያያ ገንዘብ ኒያራ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በ70 በመቶ ቀንሷል።

ግብፅ በቅርቡ ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት የተሸጋገረች ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት። በወቅቱ የግብፅ ማዕከላዊ ባንክ በመጋቢት 2024 በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሬ ተመን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን የውጭ ፋይናንስ አቅም ለማሳደግ፣ ትይዩ የምንዛሬ ገበያን ለማስወገድ፣ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቅረፍ አላማ ነበረው። 

በመጋቢት 2024 ከፖሊሲው ለውጥ በኋላ የግብፅ ፓውንድ በከፍተኛ ደረጃ በመዳከም ከ37 በመቶ በላይ ዋጋውን ከአሜሪካ ዶላር አንጻር አጥቷል። አሁን ላይ አንድ የአሜሪካን ዶላር 48.3 የግብጽ ፓውንድ ነው።

ለብር አዲስ ዘመን

እንደ ናይጄሪያ እና ግብፅ ተመክሮ፤ ኢትዮጵያ ወደ ገበያ-መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት መሸጋገሯን ተከትሎ ወዲያውኑ የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል።

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መደረጉን ይፋ ባደረገ ማግስት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብር የመግዛት አቅም ከዶላር ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ መቀነሱን ገልጿል። ይህም በመቀጠል በዚህ ሳምንትም አንድ የአሜሪካን ዶላር ከ 100 በር ተሻግሯል።

ይህ የፖሊሲ ለውጥ ከብሪተን ውድስ ተቋማት በአስቸኳይ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ብድር ለማግኘት ከመንግስት ስትራቴጂ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ተነግሯል::

እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች የገንዘብ ድጋፍን ስትጠብቅ ቆይታለች። የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ያቀረበውን የብድር ጥያቄ ተከትሎ የብሬተን ውድስ ተቋማት “የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች” ሲሟሉ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አመልክተው ነበር።

ይህንን የገንዘብ ዕርዳታ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የትግራይን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች እንቅፋት አጋጥሞት ቆይቷል። ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በህዳር 2022 የተደረሰው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከአይ.ኤም.ኤፍ ጋር ድርድርን ለማድረግ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ማሻሻያ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የተለያዩ ለውጦች ተስተውለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በቪድዮ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የሪፎርም አካሉ ሆኖ ኢትዮጵያ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ፋይናንስ ድጋፍ ከአይ.ኤም.ኤፍ፣ ከአለም ባንክ እና ከተጨማሪ አበዳሪዎች እንደምትቀበል አስታውቀዋል:: አክለውም “አይ.ኤም.ኤፍ እና የዓለም ባንክ በጋራ ልዩ እና የተፋጠነ የገንዘብ ድጋፍ እየሰጡ ነው፣ ይህም በአህጉረ አፍሪካ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።” ሲሉ ተደምጠዋል::

ይህን ተከትሎ አይ.ኤም.ኤፍ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘቢ ወዲያውኑ ይለቀቃል ተብሏል::

ይህ ከተገለጸ ከ24 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ  የአለም ባንክ የስራ አስፈፃሚ ቦርድ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን ሁለተኛውን የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግንባታን ለመደገፍ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር አጽድቋል።

ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንደገለጹት ከውጪ አበዳሪዎች ገንዘብ ማግኘት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል:: ይህም ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ እና ይፋዊ በሆነው የምንዛሬ ተመን እና ትይዩ በሆኑት የጥቁር የውጭ ምንዛሪ ገበያዎች መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት ለመፍታት ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል::

እንደ እርሳቸው ገለጻ  ከአይ.ኤም.ኤፍና ከዓለም ባንክ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነው ክፍል ረዘም ያለ ጊዜ ሲጠባበቁ የቆዩ አስመጪዎችን ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) ፍላጎት ለማሟላት ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለሙያው አክለውም  “እነዚህ የአስመጪዎች  ፍላጎቶች ከተሟሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመፍታት ጥቁር ገበያን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ስለሚቻል ከዚህ ቀደም በትይዩ ገበያ የሚተላለፉ ገንዘቦችን ጨምሮ ወደ ህጋዊ የፋይናንስ መስመሮች እንዲገቡ ያስችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሄኖክ ፋሲል በበኩላቸው በገበያ ላይ የተመሰረተ የምንዛሬ ሥርዓት ፖሊሲ አውጪዎች ውጤታማ የገንዘብ ፖሊሲዎችን የማስፈጸም ችሎታቸውን በእጅጉ እንደሚያደናቅፍ ይናገራሉ:: በተጨማሪም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ወይም የወለድ ምጣኔን በማስተካከል የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት የሚደረገው ጥረት አሉታዊ በሆነ የገንዘብ መዋዠቅ ሊዳከም እንደሚችል ይሟገታሉ።

ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መዋዠቅ በወጪ ገቢ ንግዱ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ሚዛናዊ የኢኮኖሚ እድገት እንዳይኖር እንቅፋት ሊሆን ይችላል ሲሉ አብራርተዋል::

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ገበያ-መር የምንዛሬ ሥርዓት የገበያ አለመረጋጋትን እንደሚያመጣም አበክረው ይገልጻሉ።”ለምሳሌ አንድ ባለሀብት ለአምስት አመት ፕሮጀክት ከባንክ ብድር ለማግኘት ቢያቅድ የምንዛሪ ተመን መዋዠቅ ኢንቨስትመንታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል እና ወደ ኪሳራ ሊያመራቸው ይችላል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ሊያሻሽል የሚችል ቢሆንም፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና ተጨባጭ ውጤቶችን ለማምጣት ቢያንስ ሁለት ዓመታት አስፈላጊ መሆኑን ልምድ ያላቸው አንጋፋ የኢኮኖሚ ባለሙያ ጠቁመዋል።

የውጭ ምንዛሬ ልዩነቱ እየሰፋ፤ የዋጋ ግሽበቱ እያሻቀበ መምጣት

በባንክ እና ትዩዩ በሆነው ጥቁር ገበያ መካከል ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ለኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የኢኮኖሚ ማሻሻያው በህጋዊው የምንዛሬ ተመን እና በጥቁር ገበያው መስመር መካከል ያለውን ልዩነት ሊያጠብ ቢችልም በተለይ ከሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አንጻር ግን በኑሮ ውድነት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ሊፈጠር እንደሚችል ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ መርድ የብር የመግዛት ዋጋ መዳከም ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች ከፍተኛ ወጪን እንደሚያስከትል ይገልጻሉ:: ”በተለይም አስፈላጊ የሆኑ እቃዎች ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ በሆኑበት ሀገር ለንግድ ድርጅቶች እና ሸማቾች ስጋት ሊፈጥር ይችላል” ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም “አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቋሚ ገቢ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሰዎች በቁጥር ከፍተኛ በመሆናቸው ይህ የዋጋ ንረት በኑሮ ውድነት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ወደ ለሌሎች ማህበራዊ-ፖለቲካዊ ቀውሶች ሊያዳርግ ይችላል” ሲሉ አሳስበዋል።

በተጨማሪ ነጋዴዎችም ሸቀጦችን በመደበቅ በገበያው ላይ ሰው ሰራሽ የሆነ እጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል:: ይህም የዋጋ ንረትን በማባባስ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን አቅርቦት እንደሚያስተጓጉል እና በህዝቡ ላይ ግልጽ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ሸክም እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ባለሙያው አክለው ተናግረዋል:: ይሁን እንጂ እነዚህ ማስተካከያዎች በተለይ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ አስከትለዋል።

የኢትዮጵያ ብር ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የዋጋ ቅናሽ ተደርጎበት የነበረ ሲሆን እነዚህ የዋጋ ቅነሳ ፓሊሲዎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የማበረታታት ዋና ዓላማ ይዘው ተተግብረዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ማስተካከያዎች በተለይ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ አስከትለዋል።

የአገሪቱ የዋጋ ንረት እየተባባሰ መምጣቱ በሸማቾች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል::  ይህን ተከትሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የብር ዋጋ ማሽቆልቆል ህብረተሰቡን ለተጨማሪ የዋጋ ንረት ያጋልጠዋል በሚል በባለሙያዎች ዘንድ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል።

ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛ የሆኑት አቶ ደረጀ ተስፋዬ “አዲሱ ፖሊሲ ባይኖርም ህይወታችን በአስደንጋጭ የዋጋ ንረት ተጎድቷል፤ ይህ ማሻሻያ ደግሞ ተግዳሮቶችን ይበልጥ ያባብሳል::”  ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተመዘገቡ ሶስት ልጆች አሉኝ፤ እንደ ምግብ፣ አልባሳት፣ መጽሐፍት እና የትምህርት ቁሳቁስ ያሉ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል::” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የሀገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ ዋጋ መውረድ ለቀጣይ የዋጋ ጭማሪ እንደ ዋና አቀጣጣይ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ይህም በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ከውጪ ለሚገቡ እቃዎች በሚወጣው ወጪ እንደሆነ ያስረዳሉ::

“በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን ከመከተል ይልቅ ቀስ በቀስ የብር ዋጋን መቀነስ በብዙ ምክንያቶች የተሻለ ይሆን ነበር::” የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ እና በአለም ባንክ ኢትዮጵያ አማካሪው ዶ/ር ሄኖክ ፋሲል

ባሳለፍነው ሳምንት በዋና ከተማዋ በሚገኙ ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት ደብቆ ማከማቸት እየታዩ መምጣታቸው ግምቶቹ እውን እንዲሆኑ አስችሏል። የምግብ ዘይት ዋጋ እስከ 400 ብር መጨመሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ምንም እንኳን ትክክለኛውን ተፅእኖ ለመለካት ዝርዝር ጥናት ቢያስፈልግም ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ዋጋ እየጨመሩ በመምጣታቸው አጠቃላይ የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስና እና በድሆች ቤተሰቦች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ተጽእኖ እንደሚኖረው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ሄኖክ ይገልፃሉ። አክለውም “እንደ ነዳጅ እና ምግብ ያሉ አስፈላጊ ሸቀጦች በብር ዋጋ መውረድ ምክንያት በእጅጉ ውድ ሲሆኑ ለእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚወጣው ተጨማሪ ወጪ ደግሞ ለሸማቾች ይተላለፋል::” ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ::

እንደ ዶ/ር ሄኖክ ገለጻ፣ “ከገቢያቸው ሰፋ ያለውን ክፍል ለአስፈላጊ ዕቃዎች የሚመድቡት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አባወራዎች የበለጠ የከፋ ተፅዕኖ የሚደርስባቸው ሲሆን ይህም ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር እና የድህነት አዘቅት ሊወስዳቸው ይችላል” ብለዋል:: በተጨማሪም ይህ የዋጋ ንረት ጫና አሁን ያለውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነት ሊያባብስ እና ህብረተሰቡን ሊጎዳ እንደሚችል ተናግረዋል::

በቅርቡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም መዳከሙን ውይም ወደ ገበያ-መር የምንዛሬ ተመን ሥርዓት መሸጋገሩን አስመልክቶ ስጋቱን ገልጿል::

የዓለም የምግብ ፕሮግራም “ይህ አካሄድ በህጋዊው የምንዛሬ ተመን እና ትይዩ በሆነው የጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያዎች መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ለመፍታት እንደ ስትራቴጂ የተወሰደ ቢሆንም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንደ ማዳበሪያ እና ነዳጅ ያሉ የምርት ግብዓቶች ወጪዎችን ከፍ ሊያደርግ ይችላል::” ሲል አሳስቧል::

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ መዘዙ በአገር ውስጥ የምግብ ምርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር እና በመጨረሻም የምግብ ዋጋ መጨመር ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል:: ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ የድሃ ቤተሰቦችን ህይወት የሚጎዳ እና ለብዙ ኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል የዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ገልጿል።

የመንግስት አካላትም ሁኔታው ​​ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤት አምነዋል:: ብሔራዊ ባንክ መንግሥት የሚጠበቀውን የዋጋ ግሽበት ለማቃለልም ለመንግስት ሰራተኛው የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ይህም ውሳኔ  የበጀት ጉድለቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሳያባብስ ተግባራዊ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል::

ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው እንዳመላከተው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በገጠርና በከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የምርታማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል እና ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

በቅርቡ መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ በሸቀጦች ላይ አለአግባብና ወቅቱን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና አለአግባብ ምርት ባከማቹ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ በሸቀጦች ላይ አለአግባብና ወቅቱን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ እና አለአግባብ ምርት ባከማቹ  በርካታ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል::

አንዳንድ ባለሙያዎች መንግስት በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን ከመከተል ይልቅ ቀስ በቀስ የብር ዋጋን የመቀነስ ስትራቴጂ መከተል ነበረበት ሲሉ ይሞግታሉ:: ይህም ሀገሪቱን ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እና ለወጪ መናጋት ሊያጋልጥ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል::

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ሄኖክ ፋሲል በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ::በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን ከመከተል ይልቅ ቀስ በቀስ የብር ዋጋን የመቀነስ ስትራቴጂ መከተል ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ሲሉ ባለሙያው ይገልጻሉ::

በመጀመሪያ ደረጃ፣ይህ ስትራቴጂ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቋረጥን በመቀነስ ነጋዴዎች እና ሸማቾች ከሁኔታው ጋራ ለመላመድ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላል። ይህ አካሄድ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ድንገተኛ የዋጋ ግሽበትን መከላከል ይችላል ሲሉ ገልጸዋል::

በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህን ስትራቴጂ መከተል ከዓለምአቀፉ የገበያ መዋዠቅ የሚከላከል ይሆናል ይላሉ ባለሙያው::

እንደ ባለሙያው ገለጻ በድንገት ወደ ገበያ መር የምንዛሬ ሥርዓት መግባት ድንገተኛ የገንዘብ መለዋወጥ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ያመጣል ሲሉ ይገልጻሉ:: ”ይህ አለመረጋጋትም የኢንቨስተሮችን እምነት ሊያዳክም እና ፖሊሲ አውጪዎች ውጤታማ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ለመተግበር ያላቸውን አቅም ሊያደናቅፍ ይችላል::” ሲሉ አስረድተዋል::

በተጨማሪም ባለሙያው “ቀስ በቀስ  የሚደረግ የብር ዋጋ ቅነሳ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ እንዲገባ እና እንዲቆጣጠር በማድረግ ለላቀ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት አስተዋፅዖ ያደርጋል።” ሲሉ ይገልጻሉ::

ባለሙያው አክለውም “ይህ የገንዘብ ማስተካከያ ሂደት ከሀገሪቱ ሰፊ የኢኮኖሚ አላማዎች እና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የልማት ስራዎች ጋራ መጣጣሙን ማረጋገጥ ይችላል” ሲሉ አጠቃለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button