ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “ጽንፈኛ ታጣቂዎች በሰሜን ጎጃም ዞን በርካቶችን ገድለዋል 13 የሚሆኑትን አስረዋል” ሲል የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም፡- “ጽንፈኛ ታጣቂዎች በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ ልዩ ስሙ ገርጨጭ በሚባል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የሀይማኖት መሪዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና እናቶችን በእንብርክክ በማስኬድ ኢ-ሠብዓዊ የሆነ ቅጣት በመቅጣት ግድያ ፈጽመዋል” ሲል የክልሉ መንግስት ኮነነ።

“ታጣቂዎቹ የአከባቢው ነዋሪዎቹን የገደሏቸው ለተለያዩ ስራዎች ወደ ባህርዳር ተጉዘው ሲመለሱ የሰላም ኮሚቴ አባላት ለመሆን ነው” በሚል ምክንያት መሆኑ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከተገደሉት በተጨማሪ 13 የሚሆኑ አሁንም በታጣቂዎቹ ታስረው ይገኛሉ ብሏል።

የአማራ ክልል መንግስት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ድርድር እንዲካሄድ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆመው የክልሉ መንግስት መግለጫ ከነዚህም መካከል በቅርቡ የተቋቋመው የሰላም ኮሚቴ እንቅስቃሴን በአብነት አስቀምጧል።

በክልሉ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል በተላየዩ ግዜያት በመንግስት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሰላም ለማውረድ የውይይት መድረክ ለማመቻችት ዝግጁ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ካውንስሉ ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለድርድርና ውይይት እንዲዘጋጁ የማመቻቸት ሚና ያለው ነው፤ የካውንስሉ ዓላማ ማመቻቸት ነው፤ አደራዳሪም ተደራዳሪም አይደለም ሲሉ ሰብሳቢው አቶ ያየህይራድ በለጠ በተለያዩ መድረኮች ባስተላለፉት መልዕክት ሲገልጹ ተደምጠዋል፤ ሁለቱ ወገኖች የሚፈልጉትን አደራዳሪ መርጠው በሚፈልጉት ቦታ ተገናኝተው ውይይትና ንግግር እንዲያደርጉ የማመቻቸት ሥራ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል።

ትላንት ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰሜን ጎጃም አስተዳደር ዞን የተመረጡ የሰላም ካውንስል አባላት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ማካሄዳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያሳያል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በመድረኩ የሰላም ካውንስሉ አባላት ከሁሉም የሰሜን ጎጃም ወረዳዎችና ከባሕር ዳር ከተማ የተሰባሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በመግለጫው ከተገደሉት ሰዎች መካከል የወረዳው ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጁ መርጌታ ግሩም፣ የሀገር ሽማግሌ አቶ አዘነ አድማሱ፣ የሀገር ሽማግሌ አቶ አስማማው አቤ፣ ወ/ሮ የኔአየሁ ዳኛው የተባሉ የከተማው ነዋሪዎች ይገኙበታል ሲል በዝርዝር አቅርቧል።

የታጣቂዎቹ ዋና አጀንዳ “ህዝባዊ ሳይሆን በትግል ስም ከተሳካ ስልጣን የመያዝ ካልተሳካ ደግሞ ህዝብን በመዝረፍ ንብረት አካብቶ መኖር መሆኑን በግልፅ ያሳየ ነው” ሲል ገልጿል።

ህዝቡ ድርጊታቸውን እንዲያወግዘ ጠይቋል።

የክልሉ መንግስትም በነዋሪዎቹ ላይ በተፈጸመው ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለህግ እናቀርባለን ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button