ዜና፡ መንግስት በአማራ ክልል በወሰደው የአየር ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ በጥቃቱ ኢላማ ከተደረጉ ቦታዎች መካከል ትምህርት ቤትና መነሃሪያ ይገኙበታል፡ የተባሩት መንግስታት ድርጅት

አዲስ አበባ፣ ሀዳር 8/ 2016 ዓ/ም፦ መንግስት በአማራ ክልል በወሰደው የአየር ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ በጥቃቱ ኢላማ ከተደረጉ ቦታዎች ማካከል ትምህርት ቤትና መነሃሪያ ይገኝበታል ሲል ትላንት ህዳር 7/ 2016 ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል የድሮን ጥቃቶች የሚያደርሱት አውዳሚ ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን የገለጸው ተመድ ጥቅምት 26 በዋደራ ወረዳ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ላይ በመንግስት ሃይሎች በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት መምህራንን ጨምሮ 7 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋብር ከተማ በመነሃሪያ ላይ ጥቅምት 29 በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ባስ በመጠባበቅ ላይ የነበሩ 13 ሰዎች እንደተገደሉ ገልጿል፡፡ የአየር ጥቃቱ በተፈጸም ወቅት የፋኖ ታጣቂዎች ባካባቢው እንደነበሩና በደብረ ማርቆስ የሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይና በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞን በምተገኝ ከተማ ጥቃት ማድርሳቸው ተመድ አስታውቋል። 

ህዳር 4 ቀን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቹዋሂት ከተማ ውስጥ የመንግስት ታጣቂዎች በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት 6 ሰዎች ሲሞቱ 14 ሰዎች ቆስለዋል። አብዛኞቹ ሰዎች የተገደሉት በቤታቸው ውስጥ ነው ብሏል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ በደቡብ ጎንደር ዞን ዓለምበር ከተማ መስከረም 28 እና በአዊ ዞን ጂባይት ወረዳ ጥቅምት 17 የፋኖ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና የገዢው ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 21 ሰዎች እንደተገደሉም ጠቅሷል።

ተመድ በሰሜን ምዕራብ አማራ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የቀጠሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዘፈቀደ እስሮች አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጿል። ሁሉም ወገኖች ከሕገወጥ ጥቃቶች እንዲቆጠቡ፣ የሲቪሎችን ደኅንነት እንዲጠብቁ ጠይቋል። በተጨማሪም መከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቹ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ግዴታዎች በተሟላ መልኩ መከናወን አለባቸው ብሏል። አስ

Exit mobile version