አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/ 2017 ዓ/ም፦ በመሬት መንቀጥቀጥ ውድመት የደረሰበት ከሰም ስኳር ፋብሪካ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞቹን እስከ ሶስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚያሰናብት ማስታወቁን ተከትሎ የፋብሪካው ሰራተኞች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ አንድ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኛ፤ ፋብሪካው የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም “ከስራ ገበታችሁ ለቃችኋል” የሚል ማስታወቂያ መለጠፉን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ሆኖም ፋብሪካው ማስተካከያ በማድረግ ሰራተኞች እንደየስራ ዘመናቸው ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር በሚደርስ ጊዜ ውስጥ የስራ ውላቸው እንደሚቋረጥ ቅድመ-ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ጠቁመዋል።
ማስታወቂያው የተለጠፈው ሰራተኛው ምንም ባልተዘጋጀበት እና በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ መጠለያ ውስጥ ተጠልሎ ባለበት ወቅት መሆኑ ቅሬታ ማስነሳቱን አክለው ገልጸዋል።
“ፋብሪካው መጀመሪያ አሰናብቻለሁ ነበር ያለው፤ ከዛ ግን እንደየ ስራ ዘመናቸው የሚል ነገር አመጡ። ለምሳሌ ከአምስት አመት በታች የሰራ የአንድ ወር ጊዜ ነው ያለው። ከአምስት እስከ አስር ዓመት ለሰሩ ደግሞ የሁለት ወር ጊዜ ነው የተሰጣቸው። ከአስር ዓመት በላይ ለሰሩ ሰራተኞች ደግሞ ሶስት ወር የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸዋል” ሲሉ ሰራተኛው ተናግረዋል።
በፋብሪካው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ውስጥ ተመድበው ለ11 ዓመታት ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት እኚሁ ግለሰብ የፋብሪካውን ውሳኔ “ወቅቱን እና የሰራተኛውን ሁኔታ ያላገናዘበ” ሲሉ ተችተዋል።
“የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ ሶስት ልጆች አሉኝ። እኛ በአሁኑ ሰዓት ሃሳባችን ስለመሬት መንቀጥቀጡ እንጂ በአንዴ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ይኖራል ብለን አልጠበቅንም። ሰራተኛውም በአብዘሃኛው እቃ በማጓጓዝ ብሩን ጨርሷል። ቤት ተከራይተው የሚኖሩም አሉ። እዚህ መጠለያ ያለው የኑሮ ሁኔታም ሲታይ ልብ ነው ሚሰብረው። ሰራተኛው ብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያለው። ቢያንስ ይሄን ነገር ሲወስኑ ሰራተኛው ምን ውስጥ ነው ያለው የሚለውን ከግንዛቤ ማስገባት ነበረባቸው። ግን እንደዋዛ ሊሸኙን ነው ያሰቡት” ብለዋል።
ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፋብሪካው ሰራተኛ በበኩላቸው በአፋር ክልል በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተነሳ ታኅሳስ 20 ቀን 2017 ዓ.ም አከባቢያቸውን ለቀው አዋሽ አርባ በሚገኘው እና “አዲስ ራዕይ” በተሰኘው መጠለያ ሸራ ዘርግተው እየኖሩ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ሆኖም በዚሁ መጠለያ ሆነው የሚሰሩበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከየካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ 1100 የሚሆኑ ሰራተኞችን የስራ ውል ማቋረጡን የሚገልጽ ማስታወቂያ ማውጣቱን እንደሰሙ ገልጸዋል።
ከተዘረዘሩት መካከል ስማቸው እንደሚገኝ የገለጹት እኚሁ ግለሰብ ይሁን እንጂ የሰራተኛ ማህበሩ ከፋብሪካው አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን ተከትሎ የለጠፉትን ማስታወቂያ አስተካክለው ሰራተኛው እንደሰራበት የስራ ዘመን እስከ ሶስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የስራ ውል እንደሚቋረጥ አስታውቀዋል ብለዋል።
አያይዘውም የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ መኖሩን ገልጸው በፋብሪካው ለ11 ዓመታት ያህል ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም “ያለንበት መጠለያ መጥቶ ማንም የደረሰልን ሆነ የጠየቀንም የለም። ሰራተኛው አሁን ግራ ተጋብቶ ነው ያለው።” ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል።
በፋብሪካው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው እና አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው ማስታወቂያ፤ “በተደጋጋሚ በተከሰተው ርዕደ መሬት በፋብሪካው ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ” እና በዚህ ምክንያት “ስራውን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ በመሆኑ”፤ በማስታወቂያው ስማቸው የተዘረዘረ ሰራተኞቹ የስራ ውል ከየካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ “በቅደመ ማስጠንቀቂያ” መቋረጡን ይገልጻል።
ሆኖም ፋብሪካው ይህን በማስተካከል ሰራተኞች እንደየስራ ዘመናቸው ከአንድ እስከ ሶስት ወር ቆይታ የቅድመ- ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ሰራተኞች ገልጸዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገራቸው የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሰራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጌታሁን አርሲጮ በበኩላቸው ፋብሪካው 1135 የሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞችን እና 34 የኮንትራት ሰራተኞችን የስራ ውል ከየካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደየስራ ዘመናቸው ቆይታ እስከ ሶስት ወር በሚሞላ ጊዜ ውስጥ የስራ ውላቸውን እንደሚያቋርጥ ማስታወቁን አረጋግጠዋል።
“አሁን ላይ ሰራተኛው ተረብሾ ነው የሚገኘው” ያሉት ሊቀመንበሩ ሌሎች አማራጮች እያሉ እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
ለአብነትም በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለተዘጉት እንደ ወልቃይት፣ ተንዳሆ እና አርጆ ዴዴሳ መሰል ስኳር ፋብሪካዎች ሰራተኞች የታዩ አማራጭ መፍትሔዎች ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞችም ሊታይ ይገባ ነበር ብለዋል።
በተጨማሪም ፋብሪካው 20,000 ሄክታር መሬት ሊያለማ የሚችል በቂ የከሰም ግድብ ውሃ እና ተስማሚ የአየር ንብረት እያለ፤ ሰራተኞችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ሰብሎችን (Cash Crops) እያለሙ እንዲቆዩ ማድረግ እየተቻለ ሠራተኛውን በዚህ ሁኔታ ከስራ ገበታው ማፈናቀል አግባብ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም የሰራተኛ ማህበሩ ለኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ጨምሮ ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ መጻፉን ገልጸው ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የፋብሪካውን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረኘው ጥረት ባለመሳካቱ አስታየታቸውን ማከተት አልተቻለም።
በአፋር ክልል በገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳቶችን ያስከተሉ ትላልቅ አደጋዎች መደረሳቸውና የድርጅቱ ኃይል ማከፋፈያ ህንጻ መፍረሱ ተገልጿል። የኤሌክትሪካል እና መካኒካል ጉዳቶችም መደርሳቸውን የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አሊ ሁሴን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በወረዳዎቹ ከሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ 4 ሺህ የከሰም ሱካር ፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑም ክልሉ አስታውቋል።አስ