አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/ 2017 ዓ/ም፦ በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካክለ እየተካሄደ ባለው ግጭት እንዲሁም በድርቅ፣ እና በበሽታዎች ምክንያት ተጽዕኖ ውስጥ የሚገኘውን አማራ ክልል መልሶ ለመገንባት 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ አምባሳደሮችና አጋር አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የክልሉ የሰብዓዊ ደጋፍ እና የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ግምገማና የምክክር መድረክ ላይ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ መድረኩ የክልሉን አኹናዊ ኹኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅና የሰብዓዊ ርዳታን ለሕዝባችን ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ወሳኝ ነው ሲል ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ውስጥ የዘለቀው ግጭት ትልቅ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።።
በአማራ ክልል በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካክለ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና በጦርነት ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ አስታወቋል።
በተጨማሪም ባሳለፍነው አመት በክልሉ ባለው የትጥቅ ግጭት፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ በታጣቂ ቡድን በደረሰ ውድመት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግስት አስታወቋል።
ዛሬ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) ክልሉ ባለፉት ዓመታት በደረሰበት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን አንስተዋል።
በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እንደሚጠይቅ ያነሱት ቢሮ ኀላፊው የክልሉ መንግሥት በየዓመቱ ለመልሶ ግንባታ በጀት መድቦ ሲሠራ ቢቆይም ከጉዳቱ መጠን አንፃር መሸፈን አለመቻሉን ገልጸዋል።
በመኾኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበራት ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።አስ