አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2017 ዓ.ም፡- የኤርትራ ሰራዊት የትግራይ መሬቶችን ተቆጣጥሮ ይገኛል፣ መውጣት አለበት ሲሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እና የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትግርኛ ፕሮግራም ጋር ባካሄዱት ቃለምልልስ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑ የትግራይ ቦታዎችን “ሻዕብያ” ሲሉ የጠሩት የኤርትራ ሰራዊት ቦታዎቹን የተቆጣጠረው የትግራይ የጸጥታ ሀይሎች ክፍት ስላደረጉለትና ስላልጠበቁት ነው ሲሉ ኮንነዋል።
“ሻዕብያ ትግራይ መሬት ውስጥ አለ፣ በትክክል አለ፤ ሻዕብያ ከትግራይ መሬት፣ ከሀገራችን ግዛት መውጣት አለበት፣ መቶ ፐረሰንት መውጣት አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።
አብርሃም (ዶ/ር) “ከፐሪቶርያው ስምምነት በኋላ የተነጋገርነው ጉዳይ ሁሉም ከመከላከያ ሰራዊው ውጭ የሆኑ አካላት ከትግራይ መሬት እንዲወጡ ነው፤ ሻዕብያም ገብቶባቸው ከነበሩት ሰፊ የትግራይ መሬቶች እንዲወጣ ነው የተደረገው” ሲሉ አስታውሰዋል፤ “ሄዶ ሄዶ ድንበር አከባቢ መንቀሳቀስ ጀመረ” ብለዋል።
አክለውም ትግራይ ውስጥ ያሉ አካላት “ሻዕብያ መሬታችንን ወሮ ይዟል ይላሉ፤ ከያዛቸው አከባቢዎች ገለል እንዲል፣ እንዲሁም አንዳንድ ባዶ የሆኑ የድንበር አከባቢዎችን የጸጥታ ሀይል ተቀምጦ እንዲጠብቀው ለማድረግ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ግን አያደርጉም” ሲሉ ተችተዋል።
“ይህ ማለት ግጭት ይቀስቀስ ማለት አይደለም፣ ምንም ከግጭት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም” ያሉት ሚኒስትሩ “ክፍት የሆኑ አከባቢዎች ሊሸፈኑ ይገባል፤ የፌደራል ሀይል በተስማማንበት መሰረት ወደ ድንበር አከባቢ እስኪመለስ የትግራይ የጸጥታ መዋቅር ወደ አከባቢዎቹ ተንቀሳቅሶ ቦታዎቹን ይዞ ማኔጅ እያደረገ መቆየት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም “እኛ ልንገባ ስንል አትግቡ፣ እራሳቸሁ ጠብቃችሁት ቆዩ ሲባል አይጠብቁም፤ ግን ክስ እየከሰሱ ይውላሉ፤ ይህ ጨዋታ ነው” ሲሉ ኮንነዋል።
“እኛ የምንፈልገው የጀመርነው የዲዲአር እና የኖርማላይዜሽን ስራ ቢፈጥንልን፣ ድንበር የመጠበቅ ችግር (በፌደራል በኩል) አለ ብየ አላምንም፣ አይኖርምም” ሲሉ ገልጸዋል።
“እኛ መጥተን ተጠግተን ያ የወረረው ሀይል እነዛ የድንበር ቦታዎች ላይ ይቆያል የሚል እምነት የለኝም” ያሉት ሚኒስትሩ “ቢቆይም እንኳ ልክ ለማስያዝ የሚቸገር ሀይል የለንም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“እና ጉዳዩ (የሻዕብያ ሰራዊት) እንዲወጡ የማንፈልግ ሳንሆነ እንዲቆዩም የማንፈልግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በተመሳሳይ የመንግስታቱ ድርጅት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል ሲል ኮንኗል።
አለምአቀፉ ማህበረሰብ ሰብአዊ መብት በፈጸሙት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ግፊት እያደረገ ቢሆንም አሁንም ተጠያቂ አለመሆናቸው እንዳሳሰበው አመላክቷል።
ትላንት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው በመንግስታቱ ድርጅት 58ኛው የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ላይ ንግግር ያደረጉት የሰብአዊ መብት ጽ/ቤቱ ረዳት ጸሃፊ ኢዝሊ ብራድስ ኬህሪስ በትግራይ ሀይሎች እና በፌደራል መንግስቱ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላም ቢሆን የኤርትራ ሰራዊት በክልሉ ከተቆጣጠራቸው ቦታዎች አልወጣም ብለዋል።
በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መካከያ ሰራዊት ውጭ ያሉ ሀይሎች ከክልሉ እንዲወጡ የሚያስገድድ ቢሆንም እንኳ የኤርትራ ሰራዊት አልወጣም ሲሉ ገልጸዋል።
ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የሻከረውን ግንኙነት ወደ አደባባይ የሚያወጡ መግለጫዎች በሁለቱ ወገኖች በመስተናገድ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ከነዚህም መካከል የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በአልጀዚራ ላይ ያስነበቡት ጽሁፍ ተጠቃሽ ነው፤ ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ባስነበቡት ጽሁፍ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና የተወሰኑ የህወሓት ባለስልጣናት ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ባስተላለፉት መልዕክት “የኢትዮጵያ ውስጣዊ ቀውሶች በአስመራ ላይ ሊላከኩ አይገባም” ሲሉ ገልጸው ኢትዮጵያ ቀጣናውን “የከበቡት” ችግሮች “መፍለቂያ እና ማዕከል ናት” የሚል ምላሽ መስጠታቸው የታወሳል።
በያዝነው ሳምንት ህወሓት ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙነት እየመሰረተ ነው በሚል የሚቀርበው መረጃ ፍጹም ሀሰት እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ሲል ማስተባበሉም ይታወሳል።
በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል በፕሪቶርያ የተደረሰውን ስምምነት ዋነኛ ተዋናኝ የነበረውች አሜሪካ በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር ከተቆጣጠራቸው የትግራይ አከባቢዎች እንዲወጣ ሲያሳስቡ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በባይደን አስተዳደር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አንቶኒ ብሊንከን እንዲሁም ዘጠኝ ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት ሴናተሮች የኤርትራ ኃይሎች እንዲወጡ የሳሰቡበት ዘገባ ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳል።
በሌላ በኩል የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሒደት፣ በክልሉ የሚገኙ የአማራና የኤርትራ ታጣቂዎች ሳይወጡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል፣ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መግለጻቸውን የተመለከተ ዘገባም መቅረቡ ይታወሳል። አስ