ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሯል በማሉን ድርጅቱ አስተባበለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ከመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፤ በጃል ሰኚ ነጋሳ የሚመራው የማዕከላዊ ዞን ዕዝ ከቡድኑ ተነጥሏል መባሉን ተከትሎ የውስጥ ክፍፍል አልተፈጠረም ሲል አስተባብሏል።

ባሳለፍነው ሳምንት የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥ ጃል ሰኚ ነጋሳ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ እሳቸው የሚመሩት ቡድን በጃል መሮ ወይም ኩምሳ ዲሪባ ከሚመራው በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ድርጅት መነጠሉን ተናግረዋል። ድርጅቱ “መተዳደሪያ ህግ እና ደንብ” የሌለው ነው ሲሉም ገልጸው፤ መሪውን ጃል መሮን “አምባገነን” ሲሉ ጠርተዋል።

ጃል ሰኚ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መሪ ሆነው የተሾመው ግለሰብ የድርጅቱ ሕግ እርሱ ነው፤ ድምቡም እርሱ ነው፤ ድርጅቱም እርሱ ነው፤ ለዓመታት፣ የግል ፍላጎቱን ከድርጅታዊ መርሆች ጋር ለማስማማት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፣ ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች የበለጠ ውድቀትን ነው ያስከተሉት” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት “በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እያደረጉ የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ኃይሎች ወደ ስርዓት አልበኝነት ተሸጋግ” ሲሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት፤ ሰኚ ነጋሳ ከወራት በፊት ከቡድኑ “በክህደት ተግባር” መባረራቸውን ገልጿል። 

ጽህፈት ቤቱ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀው ሰኚ ነጋሳ “ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ” ሲል ገልጿል።  

“በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ውስጥ ምንም ክፍፍል የለም፣ በትንሹም ቢሆን። ሰኚ የቀድሞ የድርጅቱ አባል ሲሆን ድርጊቱም በመላው ኦሮሚያ በሚገኙ በሁሉም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አዛዦች የተወገዘ ነው” ሲል ጽህፈት ቤቱ አክሎ ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ቡድኑ በአመራሩ ኩምሳ ድሪባ ላይ የቀረበውን “የአምባገነንነት” ክስ ውድቅ በማድረግ፣ ሰራዊቱ የሚመራው በዋና አዛዥ፣ በምክትል አዛዥ፣ ሰባት አባላት ባሉት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና ልዩ ልዩ የስራ ድርሻ ያላቸው 57 ግለሰቦች በሚገኙበት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ስር ሆኖ መሆኑን አስታውቋል።

ቢቢሲ በዘገባው እንዳመላከተው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የማዕከላዊ ዞን አዛዥ እና ከሰባቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የነበሩት ሰኚ ነጋሳ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ውስጥ በታንዛኒያ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና በመንግስት መካከል የተደረገውን ሁለተኛ ዙር ውይይት ተከትሎ የቡድኑ የመረጃ ሃላፊ ሆነው ተሹመው ነበር።

በወቅቱ ሰኝ ሹመቱን ውድቅ በማድረግ በእርሳቸው ስር የሚገኙ ተዋጊዎችን ለማስተላለፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከቡድኑ መሪ ኩምሳ ድሪባ ጋር የተፈጠረው ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል ተብሏል።

ሰኚ ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።

በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና በመንግስት ሃይሎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው በትጥቅ የታገዘ ግጭት በኦሮሚያ ክልል የሰዎች ህይወት ማለፍ፣ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት  አስከትሏል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button