ዜናፖለቲካ

ዜና: በቀጣይ በሶማሊያ በሚሰፍረው ጦር ዙሪያ በሀገሪቱ በሰላም ማስከበር ሂደት ላይ የተሳተፉ ሀገራትን ያካተተ ምክክር ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24/2017 ዓ.ም፡- በሶማሊያ በቀጣይ በሚሰፍረው ሰላም አስከባሪ ጦር ዙሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአትሚስ (የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ) ተልዕኮ ወታደሮቻቸውን ያዋጡ ሀገራትን ያሳተፈ ውይይተ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ አሚሪካንን ጨምሮ አምስት የሶማሊያ አጋር ሀገራት ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።

የአሜሪካ፣ ቱርክዪ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬት፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኳታር በጋራ በመሆን በዋሽንግተን ዲሲ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶማሊያ ጉዳይ መምከራቸውን አስታውቀዋል፤ የሀገራቱ ምክክር ለሰባተኛ ግዜ የተከናወነ መሆኑን እና በምክክሩ ወቅት የሶማሊያ መንግስት መሳተፉንም ጠቁመዋል።

አምስቱም ሀገራት በሶማሊያ ጉዳይ በመምከር ባወጡት መግለጫ “ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና አንድነት ያላንን ድጋፋ በድጋሚ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

“በቱርክዪ ተነሳሽነት በመካሄድ ላይ ያለውን የሶማሊያን እና የኢትዮጵያን የማሸማገል ሂደትን ጨምሮ በቀጠናው ቀውስን ከሚፈጥሩ አበባሽ ነገሮች በውይይት ሊፈቱ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ሀገራቱ በዋሺንግተን ስብሰባቸው በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሽብር ቡድኖችን እየፈጠሩት ያለውን እና እየተከሰቱ ያሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸውን ያመላከተው መግለጫው በጋራ የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ዓላማዎቻቸው ዙሪያም መነጋገራቸውን አስታውቋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አጋር ሀገራቱ “የሶማሊያ ፌደራል መንግስት የሀገሪቱን የጸጥታ ሃይሎችን እና የመከላከያ ተቋማትን ብቁ፣ ሙያዊ እና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው አድርጎ ለማቋቋም ለሚያደርገው ጥረት” ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

አምስቱ አጋር ሀገራቱ በሶማሊያ የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ማብቃቱን ተከትሎ በተያዘው አመት አጋማሽ ላይ በሶማሊያ በሚሰፍረው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የማረጋጋት እና የድጋፍ ተልዕኮ የሚኖረው ጦር እቅድን፣ የማጠናቀቅ አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውንም መግለጫው አትቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ከአትሚስ (የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ) በኋላ በሶማሊያ ስለሚሰፈረው የአፍሪካ ህብረት ጦር በተመለከተ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ወታደሮቻቸውን ያሰለፉ ሀገራትን ጨምሮ በዕቅድ ሂደቱ ላይ ሰፊ የባለድርሻ አካላት ውይይት እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

ይህም “የቀጣዩ ተልዕኮ ተፈጻሚ እንዲሆን ያስችላል፣ በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ግብ እና ተግባር እንዲኖረው ያደርጋል፣ ከሶማሊያ የፀጥታ ሀይል በአቅም የተገነባ እንዲሆን ያስችለዋል፤ የተጣጣመ፣ ግልጽ የሆነ የመውጫ ስልት ያለው ተልእኮ እንዲይዝ ያደርገዋል” ብለዋል።

በመጨረሻም አምስቱ አጋር ሀገራት በሶማሊያ ለዘላቂነት ያለው ወታደራዊ ስኬቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ሀገሪቱን ለማረጋጋት የሚያስችል እቅድ አስፈላጊ ነው ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

ሀገራቱ የሶማሊያን መንግስታዊ አስተዳደርን፣ ሰብአዊ ድጋፎችን፣ የጸጥታ ሀይሉን በማቀናጀት ወደ ወታደራዊ ስራዎች እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማካተት እንደሚቻል መወያየታቸውንም ጠቁመዋል። ቀጣዩን የአምሰቱን አጋር ሀገራት ውይይት በሞቃዲሾ ለማድረግ መወሰናቸውንም አስታውቀዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button