ዜናፖለቲካ

ዜና: ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል በሚመሩት “የህወሓት ቡድን አመራር ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እጀምራለሁ” - ጊዜያዊ አስተዳደሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል በሚመሩት “የህወሓት ቡድን አመራር ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እጀምራለሁ” ሲል አስጠነቀቀ፣ የጸጥታ ሀይሉ በበኩሉ በከልሉ ምንም አይነት ረብሻ አልታገስም ሲል አስታውቋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ስርአት አልበኝነት እንዲፈጠር እየሰራ ነው ባለው የእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “የህወሓት ቡድን ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ” ሲል አስጠነቀቀ።

በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሁነው በማገልገል ላይ ያሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ አምስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላትን ከስልጣን አንስቻለሁ ሲል ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ግዜያዊ አስተዳደሩ በወጣው መግለጫ ህወሓት ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ ጉባኤ ያካሄደው የእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን “መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል” ሲል ኮንኗል።

ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ቡድኑ “በክልሉ ስርዓት አልበኝነትን ለማስፋፋትና ትርምስ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ሲል ገልጾ” ከዚህ በኋላ ግን በቡድኑ ላይ “ሕጋዊ ርምጃ” መውሰድ እጀምራሉ ሲል አስጠንቅቋል።

ህጋዊ እርምጃ በምወስደበት ወቅት “ለሚደርስ ማናቸውም ጉዳት ይኼው ቡድን እና አመራሮቹ ብቻ ተጠያቂ እንደኾኑ ህዝቡ ይወቅልኝ” ሲልም አሳስቧል።

የግዜያዊ አስተዳደሩ በትላንት መግለጫው የትግራይ ህዝብ አንድነት እንዳይላላ በሚል ሁሉንም ነገር በትግስት ማሳለፉ እንደድክመት በደብረጺዮን ቡድን ዘንድ ተወስዷ ሲል አትቶ “ቡድኑ ትላንት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በክልሉ ስርአት አልቦነት እንዲሰፍን ያለውን ፍላጎት አውጇል” ሲል ኮንኗል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን “እንዴት እና በምን ሁኔታ መንግስትነት እንደሚያዝ ጠፍቶት ሳይሆን በክልሉ ትርምስ ለመፍጠር በማለም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እየሄደበት በመሆኑ ነው ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ተችቷል።

ሁኔታውን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የትግራይ የጸጥታ ሀይል በበኩሉ “በጊዜያዊ አስተዳደሩ ዙሪያ ሁለቱም የህወሓት ቡድኖች በየፊናቸው የተላየዩ ተጻራሪ የሆኑ መግለጫ ማውጣታቸውን እና ይህም በክልሉ ህዝብ ላይ መረበሽን መፍጠሩን” አመላክቷል።

የትግራይ ጸጥታ ሃይሎች በመግለጫቸው በሁለቱ ቡድኖች በሰጡት መግለጫ ምክንያት የሚፈጠር ማናቸውም የስርዓት አልበኝነት እና የጸጥታ ችግሮች አልታገስም ሲል አስታውቆ የክልሉን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ አልፈቅድም ሲል አስጠንቅቋል።

የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ እሰራለሁ ሲል አስታውቋል።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተግባር እገባለሁ” ሲል ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የትግራይ ክልል የጸጥታ አካላት በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተመሩ ይሰራሉ ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ተከትሎ በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት “የጊዜያዊ አስተዳደሩ “የትግራይ ሰራዊትን በስሩ በማድረግ ማዘዝ አይችልም” ሲል መግለጹም ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button