ዜናፖለቲካ

ዜና: በወልዲያ ከተማ ዙርያ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ ውጥረቱ ማየሉን፣ እንቅስቃሴዎች መገደባቸውን ነዋሪዎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው ወልዲያ ከተማ እና ዙርያዋ በሚገኙ አከባቢዎች እሁድ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰዓታት ሲደረግ የቆየውን በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ተከትሎ እንቅስቃሴዎች መገደባቸውንና በአከባቢው ያለው ውጥረት እያየለ መምጣቱን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት: እሁድ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የጀመረው ውጊያ ለሰዓታት በመቆየት እስከ እኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ እንደነበረ ተናግረዋል።

“ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አከባቢ ጀምሮ የከባድ መሣሪያ ድምጾች ሲሰሙ ነበር። እስከ እኩለሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ የቀጠለ ከባድ ውጊያ ሲደረግ ነበረ።” ያሉት ነዋሪ አክለውም ከሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስቴዲየም እና ማር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ የተጠመደ መድፍ ወደ መቻሬ፣ ጃርሳ መድኃኒዓለም እንዲሁም ወደ ቃሊም አቅጣጫ ሲተኮስ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአከባቢው ነዋሪ በበኩላቸው “የፋኖ ሃይሎች” በከተማዋ በተለምዶ ጉቦ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በሚገኘው የዞኑ ማረሚያቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰፍሮ በሚገኘዉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ እንዲሁም ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ በከባድ መሳርያ የታገዘ ውጊያ መቀስቀሱን ገልፀዋል።

“ውጊያው የተጀመረው እሁድ ምሽት ላይ ነው። የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ መታየቱን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊቱ የመድፍ ድብደባ ማድረግ ጀመረ።” ያሉት ነዋሪው በእሁዱ ዕለት ውጊያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆነ በተዋጊዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት በውል እንደማያውቁ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ትናንት ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በከተማዋ በሚገኘው ሰንደይ ተብሎ በሚጠራው ገበያ አከባቢ የተኩስ እሩምታ ሲሰማ እንደነበረ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአከባቢው የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ተስተጓጉሏል ያሉት ነዋሪው በአከባቢው መጣ ሄደት እያሉ የሚስተዋሉ ግጭቶች ለነዋሪዎች ከባድ ስጋት መደቀናቸውን አመልክተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በከባድ መሣሪያ የታገዙ ውጊያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

በአከባቢው ነዋሪ የሆኑ ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ንዑስ መቀመጫ በሆነችው ባልጭ የከባድ መሣሪያ ድብደባ መፈጸሙን አስታውቀው በርካታ መኖሪያ ቤቶችም በሞርታር የጦር መሳሪያ ጥቃት ተቃጥለዋል ብለዋል።

“ሞርታር እና ሌሎች የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች በግለሰብ መኖርያ ቤቶች ላይ ሳይቀር አርፈዋል” ያሉት ነዋሪው ከባልጭ በተጨማሪ በምንጃር በርኸት እና አረርቲ በተሰኙ አከባቢዎችም ደምአፋሳሽ የሆኑ ከባባድ ውጊያዎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል በበርካታ አከባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት መካከል እየተካሄዱ የሚገኙት ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል።

ከዚህ ቀደም በመስከረም 27/ 2017 ዓ/ም በአማራ ክልል፤ በምዕራብ ጎጃምና በአዊ ብሔረሰብ ዞን ስር በሚገኙ በርካታ አከባቢዎች በከባድ መሳርያ የታገዙ ውጊያዎች ተደርገዋል ስንል መዘገባችን ይታወሳል።

እንዲሁም መስከረም 22/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል፤ ጎንደር ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ተፈጸሙ በተባለ በከባድ መሳሪያ የታገዙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 20 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከተገደሉት በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ግለሰቦችም ቆስለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button