ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት “ቀደም ሲል በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የጤና ችግሮች በወረርሽኝ መልክ እየመጡ ነው” ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የክልሉ የጤና ሥርዓቱ በአግባቡ እንዳይሠራ ኾኗል ተባለ፤ “ቀደም ሲል በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የጤና ችግሮች በወረርሽኝ መልክ እየመጡ” መሆኑም ተጠቁሟል።

ይህ የተገለጸው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ባዘጋጀው ውይይት ወቅት ነው።

በውይይቱ ላይ የስትራቴጅክ ሰነድ ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና መምህር እና ተማራማሪ እንዲሁም በኢትዮጵያ የማኀበረሰብ ጤና ማኅበር የአማራ ቻፕተር ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው “ቀደም ሲል የተቆጣጠርናቸው ችግሮች አሁን በወረርሽኝ መልክ እየመጡ ነው፤ ቀድሞውንም ደካማ የነበረው የጤና ሥርዓት በእጅጉ እየተጎዳ ነው” ብለዋል፡፡

ዓለም ካላገዘን ችግሩ እየከፋ እና እየሰፋ ይሄዳል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሙያዎች እየተፈናቀሉ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፤ ለንፁሐን ወገኖች ለመድረስ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

“ሁሉም አካላትን የምንለምናቸው ዋጋ ከፍለውም ቢኾን የጤና ተቋማቱን እንዲጠብቁልን ነው” ያሉት ፕሬፌሰር ፈንቴ “የጤና ተቋማትን ጠብቁልን፤ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ማክበር ግድ ይላል፤ ሕጎችን አለማክበር ይውል ያድር ይኾናል እንጅ ተጠያቂ ያደርጋል” ሲሉ አሳስበዋል።

በክልሉ ተከታታይ የኾነ ግጭት በመኖሩ የጤና ተቋማት ተጎድተዋል፤ የጤና ባለሙያዎች መፈናቀል እና አለፍ ሲልም የሕይዎት መስዋዕትነት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ ክልሉ በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ መቆየቱን ነው የገለጹት፤ የኮሮና ቫይረስ ያመሰቃቀለው የጤና ሥርዓት ሳይሻሻል የሰሜኑ ጦርነት በክልሉ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም አስታውሰዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሰሜኑ ጦርነት የወደመው መልሶ ሳይቋቋም በአማራ ክልል ሁሉንም አካባቢ ያዳረሰው ግጭት ተፈጠረ ነው ያሉት፡፡

አሁን ባለው ችግር የጤና አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

መንገዶች ይዘጋሉ፣ ወገኖች ያለ ስጋት ወደ ጤና ተቋማት ሄደው መታከም አይችሉም ብለዋል፡፡

የታጠቁ ወገኖችን የምንለምናቸው የጤና አገልግሎቱን የሚጠብቁ ሕጎችን እንዲያከብሩ ነው ብለዋል፡፡

ሕጻናት እና እናቶች እንዳይሞቱ፣ መድኃኒት እንዲደርስ፣ በማንኛውም ሁኔታ መንገድ እንዳይዘጋ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ የጤና ተቋማት “በምንም መመዘኛ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊኾኑ እንደማይገባ” ውይይቱን ያዘገጀው የክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።

የታጠቁ ወገኖች የአለም አቀፍ ሕጎችን፣ የጤና ተቋማትን ነጻነት እንዲያከብሩ፣  የባለሙያዎችን ደኅንነትን እንዲጠብቁ እና የሰብዓዊ ድጋፎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲደርሱ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ዘርፎች ችግሮች መከሰታቸው በስፋት ማንሳታቸውን፤ እናቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በከፋ ችግር ውስጥ እያሳለፉ ነው ማለታቸውን ከአሚኮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ታመው መታከም የማይችሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው፤ ስለ ምን ካሉ ሕሙማን በነጻነት ወደ ሕክምና ቦታ መሄድ አይችሉም፣ የጤና ባለሙያዎችም በነጻነት ሕክምና አይሰጡምና ነው ማለታቸውንም አካቷል።

የመድኃኒት አቅርቦትም በተፈለገው ልክ አይደርስም፤ በክልሉ ልብን የሚሠብሩ ነገር ግን ብዙዎች ያላዩዋቸው እና ያልሰሟቸው ችግሮች ሞልተዋል መባሉንም አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button