ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች ተደጋጋሚ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ሚሊሻዎች መካከል ውጊያዎች መደረጋቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ቅዳሜ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀስቅሶ የነበረው ውጊያ እስከ እሁድ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰዓት ድረስ መካሄዱን ገልጸዋል።

“ግጭቶች አዲስ አይደሉም። መጣ ሄደት እያሉ የሚካሄዱት ግጭቶች ቀጥለዋል” ያሉት ነዋሪው አክለውም በቅዳሜ እና እሁዱ ውጊያ ስለደረሰው ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ጉዳት በውል እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በአከባቢው በተደጋጋሚ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

አክለውም በአከባቢው በ2017 መስከረም ወር ብቻ በተካሄዱ ውጊያዎች የበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማና አካባቢው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ኮር ባካሄደው ኦፕሬሽን “የጽንፈኛ ቡድን አመራር እና አባላት ጨምሮ የጦር መሣሪያዎችን መማረኩን” በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት አስታውቋል።

በተመሳሳይ ጥቅምት ወር መጀመሪያ በክልሉ ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ “በመንግሥት ኃይሎች” ተፈጽሟል በተባለ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ አማርኛ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በወረዳው ዋና ከተማ ገርጨጭ ከጥቅምት 01 እስከ ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም. በድሮን ጥቃት እና በዘፈቀደ በተፈጸሙ ጥቃቶች ህጻናትን ጨምሮ ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶች መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የገርጨጭን ጥቃት ጨምሮ በግጭት አውድ በንጹሃን እና በሕዝብ መገልገያዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን እየመረመረ እንደሚገኝ ዘገባው አመላክቷል።

በተመሳሳይ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው ወልዲያ ከተማ እና ዙርያዋ በሚገኙ አከባቢዎች እሁድ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰዓታት ሲደረግ የቆየውን በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ተከትሎ እንቅስቃሴዎች መገደባቸውንና በአከባቢው ያለው ውጥረት እያየለ መምጣቱን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል።

በክልሉ እያተካዴደ ያለው ግጭት ስለማየሉ ሌላኛው ማሳያ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በከባድ መሣሪያ የታገዙ ውጊያዎች መደረጋቸው ነው።

በወቅቱ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ንዑስ መቀመጫ በሆነችው ባልጭ የከባድ መሣሪያ ድብደባ መፈጸሙን የገለጹት የአከባቢው ነዋሪዎች በርካታ መኖሪያ ቤቶችም በሞርታር የጦር መሳሪያ ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በመስከረም ወር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ “ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኝ” ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

ይህን ያስታወቁት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም በጋራ በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “በክልሉ ሁከት እና ብጥብጥን ለማስቆም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ችግር በሚፈጥሩ የታጠቁ ሀይሎች እና በመንግስት መዋቅር ላይ በሚገኙ አካላት እርምጃ መወሰድ መጀመሩን” ገልጸዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button