አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/ 2017 ዓ/ም፦ የዩናይትድ ኪንግደም ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚያከናውናቸውን የትብብር ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መስማማታቸውን አገልግሎቱ አስታወቀ።
ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት በዩናይትድ ኪንግደም ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6) ሀላፊ ሰር ሪቻርድ ፒተር ሙርና ልዑካን ቡድናቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተቋማት ደረጃ በሚከናወኑ የሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ተወያይተዋል ተብሏል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በውይይቱ ወቅትም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በተለይም ደግሞ የቀይ ባሕር ወቅታዊ ጉዳይ፣ የደኅንነትና ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቅንጅት ለመከላከል በቀጣይ የሚደረጉ የመረጃ ልውውጥ ስራዎችን ዳሰዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ ኢትዮጵያ የባህር በር ተደራሸርነት እንዲኖራት የጀመረቸውን እንቅስቃሴ አንዳንድ አካላት ሆን ብለው ለሀሰት ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑና ይህ ደግሞ ቀጠናው እንዳይረጋጋ እና ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን አሉታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ለሀላፊው አብራርተውላቸዋል ተብሏል፡፡
አቶ ሲሳይ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት በቀጠናው እያደገ ካለው አዲስ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በጋር መስራት እንዳልባቸውም መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በቀጠናው ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ወደ ተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀየር ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ እና እንደምትወጣም ጭምር ለዩናይትድ ኪንግደም ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6) ሀላፊ ማረጋገጣቸውም ተጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከቀጣናው ሀገራት እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትና ዓለምአቀፍ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር “ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ፣ የአጋርነትና የትብብር ሥራዎቹን እየሰራ” መሆኑን የገለፁት አቶ ሲሳይ ቶላ፤ ከዩናይትድ ኪንግደም ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ጋር ያለውን ትብብርም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርና ማጠናከር እንደሚፈልግ መግለፃቸውን መረጃው አመላክቷል፡፡
የኤም አይ ሲክስ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ሀላፊ ሰር ሪቻርድ ፒተር ሙር በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተቋማቸው በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረገ ያለውን የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ መስኮች የጀመራቸውን የትብብር እና አጋርነት ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል” ማረጋገጣቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ አመልክቷል።አስ