አዲስ አበባ፣ ህዳር 12/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እገታ እና የነፍስ ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ ጽኑ እስራት ውሳኔ መሰጠቱ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዲትን የዘጠኝ ዓመት ሕፃን አግተው “ከነሕይወቷ በወራጅ ወንዝ እንድትወሰድ” አድርገዋል የተባሉና ገንዘብ የጠየቁ ሦስት ወንጀለኞች ከ21 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን ዶቼ ቬለ ዘግቧል።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ሲሆን ግለሰቦቹ ኬብሮን ደርበው የተባለችን የዘጠኝ ዓመት ህፃን ከቤት በማስወጣት አፏን በጨርቅ አፍነው ሲያሰቃዩ ከዋሉ በኋላ ምሽት 1:30 ላይ ህጻኗን ቀያ ወደ ተሰኘ ወንዝ ወስደው ከነሕይወቷ እንደጣሏት ተገልጿል።
ወንጀለኞቹ ህጻኗ በወንዝ እንድትወሰድ ካደረጉ በኋላ ለማስለቀቂያ በሚል አንድ ሚሊየን ብር ጠይቀው እንደነበረ የታዳጊዋ ወላጅ አባት አቶ ደርበው ተፈራ ገልጸዋል።
ፖሊስ ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽን በ21 ዓመት እንዲሁም ሁለተኛና ሶስተኛ ተከሳሽን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ሆለታ ከተማ የሰባት ዓመት ታዳጊን አግተው በሚሊዮን የሚቆጠር የማስለቀቂያ ገንዘብ የጠየቁ ሥስት ግለሰቦች 11 ዓመት ጽኑ እሥራት እንደተፈረደባቸው የአሜሪካ ድምጽ በዘገባው አመልክቷል።
ሶስቱ ግለሰቦች የእገታ ተግባሩን የፈጸሙት ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን ከቀኑ 8 ሰዓት አከባቢ ሰባምቦ ጌታሁን የተባለ የሰባት አመት ታዳጊን ከሱቅ ሲመለስ መንገድ ላይ አፍነው በባጃጅ መውሰዳቸው ተገልጿል።
ወንጀለኞቹ ራሳቸውን በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት አርገው በማቅረብ ለማስለቀቂያ የሚሆን አንድ ሚሊየን ብር መጠየቃቸው ተመላክቷል።
ከታጋች ቤተሰቦች ጥቆማ የደረሰው ፖሊስም ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የምዕራብ ሸዋ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ግለሰቦቹ እያንዳንዳቸውን በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።አስ