“መንግስት ሶስት የሲቪክ ድርጅቶችን ማገዱ በሲቪክ ማህበራት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት አጉልቶ ያሳያል፣ የሚወገዝ ተግባር ነው” – አምነስቲ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 18/2017 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ትላንት ህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች አመራሮች የሚደርስባቸውን ዛቻና ማስፈራሪያ በመሸሽ አገር ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳሩን ሊያጠቡና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ምልክቶችን እየታዩ መሆኑን የገለጸው ማዕከሉ “መንግስት አፋጣኝ እልባት እንዲሰጣቸው” ሲል አሳስቧል።
የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን በቅርቡ ያገዳቸው የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች “ከእገዳው በፊት የተሰጣቸው ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ፣ በግልጽ የተካሄደባቸው ምርመራ አለመኖሩ” ነግረውኛል ያለው ማዕከሉ “አካሄዱን ህግን ያልተከተለ፣ ግልጽነት የጎደለው እና በድርጅቶቹ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ድንጋጤን የፈጠረ ድንገተኛ ክስተት አድርጎታል” ሲል ተችቷል፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እግድ የተጣለባቸው ድርጅቶች የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ናቸው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላንት ህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የድርጅቶቹ መታገድ በሲቪክ ማህበር ምህዳር ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት አጉልቶ ያሳያል ሲል አውግዟል፤ መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ አሳስቧል።
አምነስቲ በመግለጫው የሲቪል ማህበራቱ ለእግድ የዳረጋቸው በሚል የቀረበው “ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆን” እንዲሁም “የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት” የሚሉ ውንጀላዎች “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈን መሳሪያነት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል” ሲል ተችቷል። “የፌደራል መንግስት እነዚህን የመደራጀት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጋፉ እና በምንም መልኩ መሆን ያልነበረባቸውን እነዚህን እገዳዎች በአስቸኳይ ሊቀለበስ ይገባል” ሲል ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል “ባለፉት ሦስት አመታት የሲቪክ ምህዳሩን ሁኔታ በቅርብ ሲከታተል፣ ሲያጠና እና በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ግምገማዎችንም ሲያቀርብ እንደነበር” ጠቁሞ “ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች አመራር የሆኑ ግለሰቦች በጽጥታ አካላት በአካልና በስልክ ተደጋጋሚ ወከባና ማስፈራሪያ” የደረሰባቸው መሆኑን አስታውቋል።
በማዕከሉ ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ተብሎ ከተዘረዘሩት አመራሮች መካከልም የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት መስራችና የቀድሞ የፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አጥናፍ ብርሃኔ ተጠቅሰዋል፤ በደረሰባቸው ወከባና ክትትል የተነሳ ከወራቶች በፊት አገር ለቀው ለመሰደድ መዳረጋቸውን ለማዕከሉ ማሳወቃቸውን ጠቁሟል።
የስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) ዋና ዳይሬከተር የነበሩት ወ/ሮ ኤደን ፍሰሃ እና በእሳቸው የተተኩትም ወት መሰረት አሊ እንዲሁ ተመሳሳይ ዛቻ፣ ወከባና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው አገር ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ነግረውኛል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዳይሬክተር የነበሩትና የማዕከሉ መስራችና የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ዳን ይርጋ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ በጸጥታ አካላት በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና፣ ወከባና ማስፈራሪያ የተነሳ አገር ለቀው ለመሰደድ መብቃታቸውን በጽሁፍ ገልጸውልኛል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የኢሰመጉ ሰራተኞች በሚደርስባቸው ተመሳሳይ ዛቻና ማስፈራሪያ የተነሳ ሥራቸውን ተረጋግተው እንዳይሰሩና ለመልቀቅም የተገደዱ መሆኑን ባደረግነው ክትትልና ምርመራ ለመረዳት ችለናል ሲል ገልጿል።
ማዕከሉ እነዚህ ችግሮች በቶሎ ሊቀረፉ ይችላሉ የሚል ተስፋ የነበረው ቢሆንም ምንም አይነት መሻሻል ሳይታይባቸው መቆየቱ እጅግ አሳስቦታል ሲል አስታውቋል።
የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን በቅርቡ ያገዳቸው የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች “ከእገዳው በፊት የተሰጣቸው ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ እነሱ የሚያውቁት በግልጽ የተካሄደ ምርመራ አለመኖሩ አካሄዱን ህግን ያልተከተለ፣ ግልጽነት የጎደለው እና በድርጅቶቹ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ድንጋጤን የፈጠረ ድንገተኛ ክስተት አድርጎታል” ሲል ተችቷል፡፡
በሲቪል ማህበራት ድርጅቶች እና በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችና እገዳዎች የሲቪል ማህበረሰቡን ምህዳር የሚያጠቡ፣ በቀሩት የሲቪል ማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ፍራቻን የሚፍጠሩ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚያደርጓቸውን የነቃ ተሳትፎዎችም እጅግ የሚያኮስሱ ናቸው እንደሚያምን አመላክቷል።
የሲቪል ማህበረሰቡ አባላትና በዋነኝነት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ የተቋቋሙ አካላት፣ ለሲቪከ ምህዳሩ መስፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል። አስ