አዲስ አበባ፣ ህዳር 18/ 2017 ዓ/ም፦ አለምአቀፉ ማህበረሰብ በአማራ ክልል በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከለ እያተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት እየደረሰ የሚገኘውን አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ቸል ብሎታል ተባለ።
ይህ የተገለጸው በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በትናንትናው ዕለት “የሰብአዊ ምላሽ ስልት ለአማራ ክልል: የትግበራ ጥሪ” በሚል መሪ ሃሳብ ከአለምአቀፍ የረድኤት ሰጪ ተቋማት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።
የፎረሙ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳስታወቁት በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ” መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት የጤና ተቋማትን ለከፍተኛ ውድመት መዳረጉን ጠቅሰው መድሃኒትን ጨምሮ መሰረታዊ የህክምና ግብአቶች እጥረት መፈጠሩ ሁኔታውን አስከፊ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን ገልጸው ከ1500 በላይ የሚሆን ት/ቤቶች መውደማቸውንም አመልክተዋል።
“የአደጋውን ጥልቀት ገና ሙሉ በሙሉ አልተረዳንም” ያሉት ዶ/ር ታፈረ ይህም አፋጣኝ የሆነ ትኩረት እንደሚያሻው አስታውቀዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር መለሰ ገበየሁ በበኩላቸው የአማራ ክልል በልዩ ልዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ፈተና ላይ መውደቁን ገልጸዋል።
በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘው ግጭትም በትምህርት እና በጤና ተቋማት ላይ ውድመት ማስከተሉን ገልጸው አስቸኳይ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ለአብነትም በክልሉ በምዕራብ፣ በሰሜን እና በምስራቅ ጎጃም ዞን አከባቢዎች እንዲሁም በማዕከላዊ እና በደቡብ ጎንደር ከ50 በመቶ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት 4870 ት/ቤቶች መዘጋታቸውንና 1552 የሚሆኑት ደግሞ መውደማቸውን ተናግረዋል።
ጤናን በተመለከተም ክልሉ እንደ ወባ እና ኮሌራ ባሉ በሽታዎች እየተፈተነ እንደሚገኝ በመጥቀስ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ እስከአሁን ድረስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውንና 50 ሰዎች ደግሞ ለህልፈት መዳረጋቸውን አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ጥበቃ ሚንስትር ደኤታው አየለ ተሾመ በበኩላቸው ከ2012 ጀምሮ በግጭ ምክንያት 40 ሆስፒታሎችን ጨምሮ ከ450 በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ ከ1800 በላይ ጤና ኬላዎች እንዲሁም ከ120 በላይ አምቡላንሶች ላይ ውድመት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።
“ይህ ግጭት በጤና እና በስነ-ምግብ አገልግሎት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ አስከፊ ነው” ያሉት ሚንስትር ደኤታው አክለውም አፋጣኝ የሆነ ምላሽ ያስፈልጋል ብለዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ኮሌጅ መምህር የሆኑት ፕ/ር ፈንቴ አምባው በትግራይ ከዛም በአማራ ክልል የተስፋፋውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ከደረሰው ውድመት 5በመቶ የሚሆነው ብቻ መተካቱን በመግለጽ “ክልሉ አውዳሚ ወደሆነ ጦርነት ውስጥ በድጋሚ ገብቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉትን በቁጥር ይበልጣሉ” ያሉት መምህሩ አክለውም “ኢትዮጵያ ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር እየተዘፈቀች ነው” ብለዋል።
“ነገ በጣም ሩቅ ነው።” ያሉት ፕሮፌሰሩ ተለዋዋጭ እና ልዩ ልዩ ለሆነው ፍላጎት አስቸኳይ የሆነ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በፎረሙ የፓናል ውይይት በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አሳየ ካሴ በበኩላቸው “ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በአማራ ክልል እየደረሰ ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ለምን ትኩረት ነፈገው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
አክለውም “ይህ ለምን ሆነ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ሁላችንም መሬት ላይ ያለውን የችግሩን ጥልቀት የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማቅረብ እና ሁሉም እንዲረዳው ማድረግ ይገባናል። በዚህ ረገድ በቂ ስራዎች አላከናወንም።” ብለዋል።
በተጨማሪም የችግሩን ዋነኛ ምንጭ በመረዳት ግጭቶችን ለማስወገድ ሰላማዊ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች አለምአቀፉ ማህበረሰብ በአማራ ክልል እየደረሰ ያለውን አስከፊ ቀውስ ቸል ማለቱን በመዳሰስ ለችግሩ አስቸኳይ የሆነ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በክልሉ በሚገኙ አስር የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋመ ሲሆን ትምህርት፣ ምርምር፣ ፈጠራ እና የማህበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማሳደግ በማለም ትኩረቱን በአማራ ክልል አድርጎ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። አስ