ዜናፖለቲካ

ዜና: በሶስት የሲቪክ ማህበራት ላይ የተላለፈው የዕገዳ ውሳኔ ትችት ማስተናገዱ ቀጥሏል፣ መንግስት “በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ” እሰጣለሁ ብሏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/2017 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በሰብአዊ መብቶች ላይ በሚሰሩ የሲቪክ ተቋማት ላይ መንግስት የወሰደው የእግድ ውሳኔ የሲቪክ ማህበራትን ምህዳር የሚያጠብ ነው በሚል ትችት ቀረበበት።

ትችቱን ያቀረበው በአለማቀፉ ደረጃ በሰው ልጆች ላይ የሚካሄዱ ስቃዮችን በተለይም ግርፋትን ለማስቀረት በሚል የተሰባሰቡ መንግስታዊ ያልሆን የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ኔትዎርክ የሆነው የጸረ ግርፋት አለምአቀፍ ድርጅት (The World Organisation Against Torture) ትላንት ህዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የመንግስት ድርጊት አሳስቦኛል ብሏል።

መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውሳኔውን ሊቀለብሰው ይገባል ሲልም ጠይቋል።

የማህበራቱ መታገድ በመዋከብ እና በማስፈራረት ውስጥ ሁነው ሲሰሩ የነበሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ዝም ለማሰኘትና የሲቪክ ምህዳሩን ለማጥበብ መንግስት አስከምን ድረስ ጥረት እንደሚያደርግ አጉልቶ ያሳያል ሲል ገልጿል።

“ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆን” እንዲሁም “የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት” የሚሉ ለሲቪክ ማህበራቱ መታገድ መንግስት የሰጠው ምክንያት መሰረት የለሽ እና አስገራሚ ነው ሲል ተችቷል።

ይልቁንም ባለስልጣኑ የሲቪክ ማህበራቱን ያገደው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ዙሪያ የሰጡትን የተሳሳተ አስተያየት ተመርኩዞ ነው ሲል ኮንኗል፤ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ሲል አመላክቷል።

ጠ/ሚኒስትር አብይ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሲቪክ ማህበራት ራሳቸውን ይፈትሹ፣ መርፌ የራሷን ቀዳዳ መስፋት አትችልም ሲሉ መግለጻቸውን ማለታቸውን በአብነት አስቀምጧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰብአዊ መብት ተቋማትን “የራሱን ቀዳዳ መስፋት እንደማትችል መርፌ” እንደሚመለከቷቸው ለፓርላማ አባላት መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማህበራትን  ማዋከብ፣ ማስፈራራት እንዲያቆም ሲል የጠቆመው ድርጅቱ ተቋማቱ ስራቸውን በአግባቡ ሊያሰራ የሚችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል ሲልም አሳስቧል።

በተያያዘ ዜና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እገዳ በተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ “በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ” እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች ላይ “ክትትል እንደሚያደርግ” እና በሚደርስባቸው “ግኝቶች መሠረት ግብረ መልስ” እንደሚሰጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ለጋዜጠኞች መናገራቸውነ ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

አቶ ፋሲካው፤ “ቀላል ጥፋት ከሆነ ቀላል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ‘ከባድ ጥፋት ነው’ ተብሎ እምነት ከተያዘበት ደግሞ ወደ ማገድ ደረጃ ሊደረስ ይችላል። ይህ አዋጃችን፣ ሕጋችን ላይ ያለ አሠራር ነው” ሲሉ የመሥሪያ ቤቱን አሠራር አንስተዋል።

ይሁንና ባለሥልጣኑ የሚያስተላልፈው እገዳ፤ ድርጅቱ “ጥፋተኛ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ገልፀዋል። እገዳ ከተጣለ በኋላ “ቀሪ ማጣራቶች” ተከናውነው “የመጨረሻ ውሳኔ” እንደሚተላለፍ አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ፤ ሰሞኑን እገዳ ከተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር “በዝርዝር” ንግግር ማድረጉን የገለጹት አቶ ፋሲካው፤ “በእኛ በኩል ያለውን ጉዳይ አንስተናል። በእነሱ በኩል ያለውንም ጉዳይ አንስተው ሰፊ ውይይት አድርገናል። በአመዛኙ፤ በቀጣይ ማከናወን በሚገባን ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ነው የተለያየነው” ብለዋል።

ከድርጅቶቹ በተጨማሪ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋርም ውይይት ማደረጉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የድርጅቶቹን ጉዳይ “የሚያጣራ ቡድን” ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ እና የታገዱት ድርጅቶቹም “ትብብር እያደረጉ” መሆኑንም አክለዋል።

አቶ ፋሲካው፤ የሦስቱ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት” ያገኛል ብለው እንደሚያስቡ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አቶ ፋሲካው፤ ከዚህ በፊት የታገዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጉዳይ በተመለከተም “በአንዳንድ ክስተቶች የሲቪል ምኅዳሩ በቃ ጠቧል ዋጋ የለውም ብሎ መደምደም ደግሞ ትክክል ነው ብዬ አልወስድም” ሲሉ ተደምጠዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button