አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2017 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ትላንት ህዳር 22 ቀን የሰላም ስምምነት የፈረሙት ከወራት በፊት በስነምግባር ጉድለት ካባረርኳቸው አመራር ጋር ነው ሲል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አስተባበለ።
የኦሮምያ ክልል መንግስት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥ ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግሥት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የሰላም ስምምነት ፈርመዋል ሲል መግለጹ ይታወቃል።
ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አፈንገጠው የወጡ ተደርጎ በመንግስት በኩል እየቀረበ ያለው መረጃ ፍጹም ሀሰት ነው ሲል የገለጸው መግለጫው የህዝቡን ስነልቦና ለመግዛት በሚል በመንግስት በኩል የቀረበ ማታለያ ነው ሲል ተችቷል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር ከነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል ትላንት ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በፊርማ ስነስርአቱ ላይ አቶ ሽመልስ የኦሮሞ ሕዝብ በባህሉ መሰረት ሰላም ይውረድ ብሎ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በክልሉ መንግሥት ስም አመሠግናለሁ ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦም አቶ ሽመልስ አመሥግነዋል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት÷ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለመጡት ምስጋና አቅርበዋል።
ከጦረኞች በላይ ጦርነትን የሚያባብሱት ስለጦርነት የማያውቁ ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ÷ እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መግለጻቸውን ከመከላከያ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ቡድኑ ትላንት ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ከወራት በፊት ከሰራዊቱ በስነምግባር ጉድለት የተባረሩትን አመራር ከሰራዊት ያፈነገጡ በማስመሰል የሰላም ስምምነት ፈጸምኩ ሲል ነው የገለጸው ብሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመግለጫው “ከወራት በፊት የተባረሩትን አባላት በማሰባሰብ እንድ ቪኦኤ እና ቢቢሲ የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃንን በመጋበዝ ከሰራዊቱ የከዱ በማስመሰል ዘገባ ቢያሰራም ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል ሲል”፣ አልተሳካለትም ሲል ገልጿል።
“አሁን ደግሞ ከነዚህ አካላት ጋር ሰላም ስምምነት ፈጽሚያለሁ እያለ የክልሉ መንግስት ህዝቡን እያሳሳተ ነው” ሲል ኮንኗል፤ “የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማሳሳት የተጠቀመበት ነው” ሲል ገልጿል።
የክልሉ መንግስት “መሬት ላይ ያለውን እውነታ መጋፈጥ አለመቻሉን አጉልቶ ያሳያል” ሲል አመላክቷል። አስ