ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ በዋስትና እንዲለቀቁ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/ 2016 ዓ/ም፦ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ በዋስትና  እንዲለቀቁ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መወሰኑን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ዛሬ በዋለው ችሎት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቶ ታዬ በዋስትና እንዲፈቱ መወሰኑን አረጋግጠዋል። 

በዚህም መሰረት እንዲለቀቁ የሚያስፈልጉ ሂደቶችኝ በማስፈጸም ላይ እንደሆኑን አክለው ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደኣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ታህሳስ 2 ቀን በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። 

አቶ ታዬ ደንደኣ  ታኅሣስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉት  “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር  ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ስለተደረሰባቸው” በሚል መሆኑን የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል በወቅቱ አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ታዬ ደንደአ ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቧል።

በዚህም መሰረት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ “ተከሳሹ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስትንና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው  ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ድጋፍ የሚገልጹ መልዕክቶችን  ሲያስተላልፉ ነበር” የሚል ነው፡፡

እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም  ከረፋዱ 5 ሰዓት  ላይ በልደታ ክ/ከ ወረዳ 6  በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽን ኮቭ  መሳሪያ ከ2 ክላሽ ካዝና  እና ከ60 ጥይት ጋር ይዘው መገኘታቸው ተጠቅሶ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሐምሌ 30 በዋለው ችሎት ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን በ3ኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን መሰጠቱም ይታወሳል፡፡

አቶ ታየ በሁለቱ ክሶች ነፃ መባላቸውን ተከትሎ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ቢጠይቁም ችሎቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል። 

በከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ አቶ ታዬ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. በነበረ ችሎት ይግባኝ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዕለቱ ውሎው አቶ ታዬ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄያቸውን በሁለት ምክንያቶች ማለትም፤ “የተከሰሱበት ሦስተኛው ክስ ከ8-25 ዓመታት በእስር እንደሚያስቀጣ” እንዲሁም “ተከሳሹ በሚፈለጉበት ጊዜ ፍርድ ቤት ላይቀርቡ ይችላሉ።” በሚል የታችኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን በማጽናት ውድቅ አድርጎታል።

የጦር መሳሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ሶስተኛው ክስ እንዲከላከሉ ውሳኔ የተላለፈላቸው አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ባለስልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።

በምስክርነት ካቀረቧቸው መካከል በቅርቡ ከኃላፊነት የተነሱት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።

አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚገኙ ሶሆን ምስክርነታቸውን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 3/ 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዛሬ ህዳር 23/ 2017 ዓ.ም በነበረው ችሎት ነው አቶ ታዬ ደንደአ በዋስትና እንዲለቀቁ ወስኗል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button