ዜናፖለቲካ

ዜና: “መንግስት የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሰሩ ድርጅቶችን ማዋከብ፣ ማገድ ሊያቆም ይገባል” ሲል ሂዩማን ራይት ወች አሳሰበ  

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2017 ዓ.ም፡- በሲቪክ ድርጅቶቹ ላይ መንግስት ያስተላለፈውን የእግድ ውሳኔ እንዲያጤነው በመቅረብ ላይ ያሉ የአለም አቀፍ ተቋማት ጥሪዎች እንደቀጠሉ ነው፤ ሂዩማን ራይት ዎች ትላንት ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መንግስት ሶስት የሲቪክ ድርጅቶችን ማገዱን አስታውቆ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውሳኔውን ሊቀለብስ ይገባል ሲል አሳስቧል።

“የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሰሩ ድርጅቶችን ማዋከብ፣ ማገድ ሊያቆም ይገባል” ሲል ያሳሰበው ሂዩማን ራይት ወች የሲቪክ ተቋማት በነጻነት ሊሰሩበት የሚያስችል ምህዳር እንዲፈጠር ጠይቋል።

የሲቪል ማህበረስበ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)ን ጨምሮ ሶስት የሲቪክ ድርጅቶችን ከስራ ማገዱ መዘገባችን ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊቱን በማውገዝ መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ መጠየቁን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

ከአምነስቲ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች አመራሮች የሚደርስባቸውን ዛቻና ማስፈራሪያ በመሸሽ አገር ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን በማስታወቅ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ያሳሰበበት ዘገባም ቀርቧል።

በተመሳሳይ በአለማቀፉ ደረጃ በሰው ልጆች ላይ የሚካሄዱ ስቃዮችን በተለይም ግርፋትን ለማስቀረት በሚል የተሰባሰቡ ከ200 በላይ መንግስታዊ ያልሆን የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ኔትዎርክ የሆነው የጸረ ግርፋት አለምአቀፍ ድርጅት (The World Organisation Against Torture) ህዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የመንግስት ድርጊት አሳስቦኛል ማለቱም ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት አጋር የሆኑ ሁሉም ይህንን የመንግስት ድርጊት በይፋ ማውገዝ ይገባቸዋል ሲል ሂዩማን ራይት ዎች በመግለጫው አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር “የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ገለልተኛ የሲቪክ ማህበራት የሚንቀሳቀሱበትን በሀገሪቱ ያለውን የተጣበበ ምህዳር ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ላይ ናቸው” ሲሉ መናገራቸውን አመላክቷል።

ሃላፊዋ በተጨማሪ “መንግስት በቅርቡ ያሳለፈው ሶስት ሲቪክ ተቋማትን የማገድ ውሳኔ የሚያሳየውም የመንግስትን እንቅስቃሴ ለመተቸትም ሆነ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ለመስራት ኢትዮጵያ በጣም ምቹ ያልሆነች ሀገር መሆኗን ነው ሲሉም መተቸታቸው ተካቷል።

መንግስት የቀድሞ የሀገሪቱ አገዛዞችን ተግባትር እየደገመ ነው ሲል የገለጸው ሂዩማን ራይት ዎች የቀድሞ የሀገሪቱ አገዛዞች ጨቋኝ ህጎችን በማውጣን የሰብአዊ መብት ተቋማት እንዳይነቀሳቀሱ ያደርጉ ነበር ሲል አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሲቪክ ድርጅቶቹን እገዳ በአስቸኳይ እንዲቀለብስ የጠየቀው ሂዩማን ራይት ዎች እየተባባሰ የመጣውን እርምጃውን እንዲያቆም እና የሲቪል ማህበራት የሰብአዊ መብት ተግባራቸውን በነጻነት እንዲያከናውኑ መፍቀድ አለበት ሲል ጠይቋል።

ሁኔታው የሚያሳስባቸው ሌሎች መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርሰውን ጭቆና አስመልክተው ዝምታቸውን መስበር አለባቸው ሲል አሳስቧል፤ አስቸኳይ ውግዘት ሊያስተላልፉ ይገባል፣ የሚታይ ጫና ሊያስድሩ ይገባል ሲል አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button