አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2017 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ከመከላከያ የምልመላ መስፈርት ውጪ ሕፃናትን በግዳጅ ለወታደርነት እየተመለመሉ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት ህዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ተቸ።
ኢሰመኮ በመግለጫው ባደረኩት ክትትል እና ምርመራ የ11 አመት ህጻን ለወታደርነት ሞያ ተመልምሎ በማቆያ ቦታ አግኝቸዋለሁ ሲል ጠቁሟል፤ በተጨማሪም ዳቦ ለመግዛት ከቤት የወጣ የ15 ዓመት ጨምሮ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ህጻናት ተመልምለዋል ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
የተያዙትን ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለመገደዳቸው መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ እጩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት ክትትል እና ምርመራ አድርጊያለሁ ብሏል።
ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተይዘው የነበሩ ሕፃናትን እና የአእምሮ ሕሙማንን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ለማስለቀቅ መቻሉን ጠቁሟል።
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ምልመላውን ያከናወኑት የሰራዊቱን አሠራር እና መስፈርቶች በጣሰ ሁኔታ ነው ሲል አስታውቋል።
በመከላከያ ሚኒስቴር መመሪያ መሠረት በዝቅተኛው መስፈርት በውትድርና ሙያ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆኑ፣ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቁና የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አትቷል።
ሆኖም የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች አባላት በመከላከያ ሚኒስቴር ከተገለጸው የምልመላ መስፈርት ውጪ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግዳጅ መያዛቸውን አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል።
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚህ አግባብ የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዳቸውንም አረጋግጫለሁ ብሏል።
እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ ህጻናት እንዲመለመሉ የተደረገው የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች እና የጸጥታ አካላት የተቀመጠላቸውን የምልመላ ኮታ ለማሟላት፣ ያልተገባ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ህገወጥ ተግባር መሆኑን አመላክቷል።
ኢሰመኮ በሻሸመኔ ከተማ በሁሩፋ ክፍለ ከተማ፣ ሀሌሉ ወረዳ ውስጥ በማቆያ አዳራሽ ከነበሩ እና ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል 14ቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 16 ዓመት መሆኑን መግለጻቸውን አንድ ሕፃን ደግሞ ዕድሜው 11 ዓመት መሆኑን ጠቁሟል።
ከትምህርት ቤት ሲወጡ ከነዩኒፎርማቸው ሀሌሉ ወረዳ ወደ ሚገኘው ማቆያ አዳራሽ እንዲገቡ የተደረጉ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ሁለት የ15 ዓመት ሕፃናት ወደ አዳራሽ ከገቡ ሁለት ሳምንት እንደሆናቸው ነግረውኛል ሲል ለአብነት በመግለጫው አካቷል።
ያለ ፈቃዳቸው በፖሊስ እና በሚሊሻ አባላት ተይዘው እንደገቡ፤ በአዳራሹ ከሳምንት በላይ እንደቆዩ እና መውጣት እንዳልቻሉ ነግረውኛል ብሏል።
የመንግሥት አካላት ምላሽ በተመለከተ ኢሰመኮ በመግለጫው የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን የሚያውቁ መሆኑን ገልጸውልኛል ብሏል።
አክለውም በመደለያም ሆነ በግዳጅ ሕፃናትን ጨምሮ ከመስፈርቱ ውጪ የሆኑ ሰዎችን የመለመሉ የጸጥታ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነግረውኛል ሲል ጠቁሟል።
ይህንን ተግባር የፈጸሙ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተከናውኖ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ሲል ለኦሮምያ ክልል መንግስት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “በቀጣይ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚካሔዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች ሰራዊቱ ባስቀመጠው አሠራር እና መስፈርት መሠረት በፈቃደኛነት ላይ ብቻ ተመሥርተው መከናወናቸውን ሊያረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ለወታደራዊ ስልጠና በግዳጅ የሚወሰዱ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል፤ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎች በግዳጅ ወደ ወታደራዊ ስልጠና መወሰዳቸውን በዘገባው ተካቷል። አስ