ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ የተፈናቀሉ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1/ 2017 ዓ/ም፦ በመሬት መንቀጥቀጥ አፋር ክልል በገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች ከሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ 4 ሺህ የከሰም ሱካር ፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ሰብዓዊ  ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ክልሉ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ። 

በሬክተር ስኬል እስከ 5 ነጥብ 8 የደረሰ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገቡ ማህበረሰቦች መበታተናቸውን የገለፁት የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ  አህመድ ኢብራሂም፤ “መጠለያ ውስጥ ከሚገኙት ውጪ ከብቶቻቸውን ይዘው አማራ ክልል አካባቢ ወደሚገኙ ተራራዎች የተጓዙ ሰዎችም አሉ” ብለዋል።

በንብረት ላይ ከደረሰው ውድመት ውጭ እስካሁን በሰው ህይትና አካል ላይ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ጠቁመው፣ በስምንት መጠለያ ጣቢያዎች የሰፈሩትን ተፈናቃዮች እርዳታ ለማድረስ ምቹ ወደ ሆነ አንድ ማዕከል የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አሊ ሁሴን በፋብሪካው ላይ የደረሰውን አደጋ የሚመረምር ከሁሉም ዘርፍ ሙያተኞች  የተካተቱበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደሥራ መግባቱን ገልጸው የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅም ዝርዝር ጉዳቱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡

በፋብሪካው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳቶችን ያስከተሉ ትላልቅ አደጋዎች መድረሳቸውን የተናገሩት አቶ አሊ፤ የድርጅቱ ኃይል ማከፋፈያ ህንጻ መፍረሱን ተናግረዋል፡፡ ኤሌክትሪካል እና መካኒካል ጉዳቶችም ደርሰዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የምርት ማቀነባበሪያ ህንጻ፣ የሰራተኞች መመገቢያ ክፍል፣ ላብራቶሪ፣ የአስተዳደር ህንጻ እንዲሁም የሰራተኞችና አመራሮች መኖሪያ መንደሮች ላይ ጉዳት ደርሷል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ፋብሪካው ሸንኮራ ልማት በሚያካሂድበት 2 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ ረጃጅም ኪሎ ሜትር የሚዘልቁ መሰነጣጠቆች መፈጠራቸውን ያነሱት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ በተለያዩ ሳይቶች በሚገኙ መጋዝኖች እና ጋራዦች ላይ ጉዳቶች መደርሳቸውንም አክለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ተጨማሪ ሊኖሩ የሚችሉ ኤሌክትሪካል፣ መካኒካል እና የሲስተም ጉዳቶች በባለሙያዎች ተጠንተው የሚቀርቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የሚያስተዳድራቸው አራት ሺህ ሰራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ከአካበቢው ተነስተው ክልሉ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት ባዘጋጃቸው የተመረጡ ቦታዎች ላይ እንዲሰፍሩ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡ 

የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ አህመድ ኢብራሂም የመሬት መንቀጥቀጡ በመንገድ አውታር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸው ከሲዲያአፋጌ መገንጠያ ወደ ከሰም ሱካር ፋብሪካ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰፋፊ ስንጥቅ፣ ስርገት እና እብጠት እንዳጋጠመው ተናግረዋል።

ስምንት የጤና ተቋመት ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ገልፀው፣ በጤና ተቋማቱ ይሰሩ የነበሩ ሀኪሞች በመጠለያ ጣቢያዎች በተተከሉ ጊዜያዊ ጤና ተቋማት ማህበረሰባቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የነብስ አድን ምግቦችን በማቅረብ፤  በቋሚነት ውሃ የሚያመላልሱ ሁለት ቦቴ መኪኖችን በመመደብ፤ በመጠለያ ጣቢያዎች 15 ሮቶዎችን በማስቀመጥ  እንዲሁም አልባሳትን በመስጠት ለተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበረሰቦችን ከአደጋ ቃጠና በማራቅ ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ በማስፈር፤ ውሃ በቦቴ መኪና በማቅረብ እና አከባቢዎችን በመጠበቅ “የህዝብ አለኝታነቱን” አስመስክሯል ብለዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button