አዲስ አበባ ጥር 3/ 2017 ዓ/ም፦ የኦሮሚያና አማራ ክልል እንዲሁም በሀገሪቱ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች ቆመው ነዋሪዎች ሰላምን እንዲያገኙ፤ በትግራይ ክልል ያለው የአስተዳዳሪዎች አለመግባባት ተፈቶ ዕረፍት ያጣው ሕዝብ መረጋጋት እንዲችል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ።
ፓትርያርኩ ትናንት ባስተላለፉት የሰላም ጥሪ የሰላም ትርጉሙ ተረጋግቶ መኖር፣ ወደ ዓላማ ፍጻሜ መድረስ፣ መርቆ ማለፍ ነው፤ ካሉ በኋላ “ወልዶ ለመሳም፣ አሳድጎ ለመዳር፣ ዐርፍተ ዘመን የጌታቸውን በክብር ለመሸኘት ሰላም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
“እስካሁን ድረስ የብዙ ነገሮች ዋጋ ታውቋል፤ የሰላም ተመን ግን አልታወቀም” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ሰላም ጠብን መግደል፣ ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ይድላው ብሎ የልብ ስፋት ማግኘት ነው ብለዋል።
“በዓለም ላይ ብዙ ሺህ የሰላም ስምምነቶች ሲደረጉ ኖረዋል። የሰው ልጅ ግን ሟች መሆኑን ረስቶ ገዳይ በመሆኑ፣ ራሱንም በራሱ ለማወክ በመፍቀዱ የሰላም ስምምነቶች ተፈርመው ፊርማው ሳይደርቅ እንደገና ሁከት ይሆናል” ሲሉ ገልጸዋል።
ፓትርያርኩ በመልዕክታቸው አንድ ዓይነት መልክና ማንነት ያለው ሕዝብ “መተላለቁ ሰውነትንም መንፈሳዊነትንም መክሰር” እንደሆነ የተረዳነው አይመስልም ሲሉ ገልጸው “በእውነቱ ካየነው ነጭ ለብሰን ሳይሆን ማቅ ለብሰን የምናለቅስበትና በንስሐ ምሕረተ ሥላሴን የምንናፍቅበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
አክለውም ትዕግሥተኛዋ መሬት እንኳ እየተናወጠች፣ ዓለም የቅጽበት ዕድል ብቻ እንዳላት እየጠቆመች ነው ሲሉ ገልጸው “የመሬት መንቀጥቀጡ የዘመኑን ፍጻሜ የሚያስረዳ ሲሆን የምናያቸው ምልክቶች ሁሉ በተሰበረ ልብ እግዚአብሔርን እንድንፈልግ የሚያሳስቡን ናቸው” ብለዋል።
በመሆኑም በሀገራችን በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች ቆመው ልጆቻችን በሰላም መኖር እንዲችሉ፤ በጦርነት እየተሰቃዩ የሕመማቸውን ልክ መናገር የማይቻለን የኦሮሚያና የአማራ ክልል ነዋሪዎች ሰላምን እንዲያገኙ አባታዊ ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን በማለት ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል ያለው የአስተዳዳሪዎች አለመግባባት በሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ችግርና ጭንቀት እያመጣ ስለሆነ በትሕትና መንፈስ እርስ በርስ መገናዘብ ተፈጥሮ ዕረፍት ያጣው ሕዝብ መረጋጋት እንዲችል ታደርጉ ዘንድ አደራችን የጠበቀ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች “መበደላችሁን እናውቃለን፣ በኀዘናችሁ ሰዓት አብረን መቆም ባለመቻላችን ማዘናችሁም እርግጥና ተገቢ ነው” ያሉት ፓትርያርኩ አክለውልም “ሁሉም ነገር የሚካሰው በእርቅ ሲሆን እኛ የገፋነውን እርቅ ዓለም ሊቀበለው ስለማይችል፤ በእጃችንም የያዝነው መስቀለ ክርስቶስ የሰላም ዓርማ ነውና ልባችሁን ለሰላም፣ ለአንድነት እንድታዘጋጁ” ሲሉ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለበት አካባቢ እየተጨነቃችሁ ያላችሁ ልጆቻችን ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ታስባችኋለች ብለዋል። አክለውም ለመላው ኢትዮጵያውያን ለጉዳቱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለሚኖሩት ወገኖቻቸው አቅማቸው በፈቀደው መጠን ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሩ አቅርበዋል። አስ