
አዲስ አበባ፣ ጥር 7/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ/ም ከማያ ከተማ ወደ ጉራዋ ወረዳ በሞተር ሳይክል በመጓዝ ላይ የነበሩ ሁለት ወጣቶች “በጸጥታ ኃይሎች” በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ቤተሰቦቻቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ግድያው የተፈጸመባቸው ወጣቶች ከዲሬ ሹኢቤ እና ጃፋር አብዱራዛቅ የተባሉ የጉራዋ ወረዳ ላፍቶ ቀበሌ ነዋሪ እንደሆኑ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከዲሬ ቤተሰብ አባል ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ወጣቶች ሰኞ ከቀኑ 8 ሰአት አዲስ ሞተር ሳይክል ለመግዛት ወደ ማያ ከተማ ሄደው ምሽት 2 ሰዓት ላይ በመመለስ ላይ እያሉ መገደላቸውን ተናግረዋል።
“ጠዋት በሰላም ወጥተው አዲስ ሞተር ሳይክል ለመግዛት ወደ ማያ ከተማ ሄዱ። ከገዙ በኋላ በሞተር ሳይክሉ ወደ ጉራዋ ላፍቶ ወረዳ እየተመለሱ እያለ በሁለት ሚሊሻዎች ጥይት ተመተው ተገድለዋል” ብለዋል።
“ሚሊሻዎቹ በጥይት ተኩሰው ካቆሰሏቸው በኋላ እዚያው ተተዋቸው እንደሄዱ” የተናገሩት የቤተሰቡ አባሉ፤ “በኋላም የአካባቢው ማህበረሰብ አምቡላንስ ጠርቶ ወደ ጉራዋ ሆስፒታል ቢወስዳቸውም ሊተርፉ አልቻሉም” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
የግድያውን መንስኤም የሟቾቹ ቤተሰቦች እስካሁን እንደማያውቁ ተናግረዋል። “እነዚህ ልጆች በጣም ትታንሽ ናቸው እና ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግጭት የላቸውም ለምን በጸጥታ ሃይሎቹ እንደተገደሉ አልገባንም። ቤተሰቡ ትልቅ ሀዘን ውስጥ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የጉራዋ ወረዳ ነዋሪ ሁለቱንም ወጣቶች እንደሚያውቋቸው ተናግረው በጥይት ተመተው መሞታቸውን አረጋግጠዋል። “እነዚህን ልጆች በጥይት ሲመቱ ባላይም፣ አስክሬናቸውን ግን በአካል ሄጄ አይቻቸዋለሁ” ብለዋል።
አክለውም “በጣም ሥነ-ምግባር ያላቸው ልጆች ናቸው። ከየትኛውም የመንግስት አካል ጋር ምንም አይነት ግጭት እንደሌላቸው አውቃለሁ። ለምን እንደተገደሉ ግን ሊገባኝ አልቻለም” ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ይህን ድርጊት የፈጸሙ የጸጥታ ኃይሎችም ሆነ ተጠርጣሪዎች እስካሁን በቁጥጥር ስር አለመዋላቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ስታንዳርድ የጉራዋ ወረዳ አስተዳደር እና የጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ አስታየታቸውን ማካተት አልተቻለም።
በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ኃይሎች ሲገደሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው አርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም በክልሉ ቦረና ዞና በሞያሌ ከተማ ሸዋ ባር ቀበሌ የ14 አመት ታዳጊ “በፖሊስ አባላት” መገደሉን ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። ግድያውን ተከትሎ የከተማው ህዝብ ባለፈው ቅዳሜ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ተኩስ ከፍቶ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዞኑ ሚዮ ወረዳ ቀላ ቦነያ የተባለ የ24 አመት ወጣት “በጸጥታ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ” ይታወቃል። ይህም ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረ ሲሆን ድርጊቱን በመፈጸም ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት የመንግስት ሚሊሻዎች መንግስት አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመስከረም ወር የጸጥታ ሃይሎች በሚዮ ወረዳ ቦኩ ሉቦማ አካባቢ በአራት ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ወቅት አንድ ወጣት ሲሞት ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። አስ