
በይስሓቅ እንድሪስ @Yishak_Endris
አዲስ አበባ፣ ጥር 8/ 2017 ዓ/ም፦ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ተከትሎ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች እየቀረበላቸው የሚገኘው እርዳታ በቂ አለመሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
አቶ ፈኪር አህመድ በዱለቻ ወረዳ ሰገንቶ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ በአከባቢው በተደጋጋሚ እያጋጠመ የሚገኘውን የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ተከትሎ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ አሚበራ ወረዳ በሚገኘው ዳኢዶ የመጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን ገልጸዋል።
“67 ኪሎ ሜትር ርቀት በእግር ተጉዤ ነው የመጣሁት። ከእኔ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች በእግራቸው እዚህ አሁን ወደምንገኝበት መጠለያ ገብተዋል። በአስፋልት የሚመጡም አሉ እነሱ ደግሞ ወደ 25 ኪ.ሜ ይሆናል የሚጓዙት።” በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
አቶ ፈኪር የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጠቅሰው ከአባት እና እናታቸው እንዲሁም ከሚስታቸው እና ከአራት ልጆቻቸው ጋራ ከአስራ ሁለት ቀናት በፊት ወደ መጠለያ ጣቢያው መግባታቸውን ተናግረዋል።
“ቤት ንብረታችንን ጥለን ነው የወጣነው ምንም ነገር ይዘን አልወጣንም” ብለዋል።
አክለውም አሁን ላይ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ይሁን እንጂ እየተደረገ ያለው እርዳታ በመጠለያ ጣቢያው ካሉ የተፈናቃዮች ብዛት አንጻር በቂ አይደለም ይላሉ።
“እርዳታ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እያገኘን ነው። በቂ ነው ማለት ግን አይደለም። ያለው የሰው ብዛት እና የሚመጣው እርዳታ ተመጣጣኝ አይደለም። የውሃ ችግር በጣም አለ። የሮቶ ውሃ ነበረ የምንጠቀመው እሱ ካለቀ በኋላ ሰው የወንዝ ውሃ ነው እየተጠቀመ ያለው አሁን ላይ። ይህም ለበሽታ ተጋላጭ እንዳያደርገን ስጋት አለን።” ሲሉ ሁኔታውን አብራርተዋል።
አቶ ፈኪር ከመጠጥ ውሃ በተጨማሪ በመጠለያ ያለ ችግር መኖሩን ያስረዳሉ።
“ሁለተኛ የመጠለያ ሸራ አቅርቦት ችግር ነው። በርካታ አቅመ ደካማ አባዎራዎችን ጨምሮ ያልደረሳቸው ተፈናቃዮች አሉ። ማደሪያ የሌለው ካለው ጋር ተጠጋግቶ ነው እያደረ ያለው።” ብለዋል።
በተጨማሪም “ባዶ እህል ነው የሚመጣው። የሚበላ ምግብ ችግርም አለ። ለምግብ ማብሰያ የሚውል ዘይትም የለም። እህል ያልደረሰው እንኳን ካለ እሱን ለሶስት ለአራት ይካፈሉና ይጠቀማሉ” ሲሉ አክለዋል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዳጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ከሰገንቶ ቀበሌ ተፈናቅለው ከሶስት ልጆቻቸው ጋር “ሰዲ ማዞርያ” በሚገኝው መጠለያ ጣቢያ መስፈራቸውን ጠቁመዋል።
በወቅቱ ለግል መኪና ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማስወጣታቸውን የገለጹት ነዋሪው አሁን ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ከሳምንት በፊት ነው መጠለያ ጣቢያው ውስጥ የገባነው። ማረፊያ ፍራሽ የለንም። ምንጣፍ አንጥፈን ነው የተኛነው። አስቸጋሪ ነው።” ያሉት ነዋሪው አክለውም በጣቢያው ውስጥ የምግብ እጥረት መኖሩን አመልክተዋል።
“ምግብ እርዳታ እየተሰጠን ነው። ነገር ግን እሱም ቢሆን በቂ አይደለም። በቅርቡ 50ኪ.ግ ዱቄት ደርሶን ነበረ። ለቤተሰብ ደግሞ በቂ አይደለም ይሄ። በጣቢያው እርዳታው ያልደረሳቸውም ሰዎች ይመጣሉ እነሱ ጋራ እንጋራለን። ይሄን ስታስብ ከባድ ነው ያለንበት ሁኔታ። ፈጣሪ መዓቱን አርግቦት ቶሎ ወደ መኖሪያችን መመለስ ነው የምንፈልገው።” ብለዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ በጣቢያው ውስጥ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያ በበኩላቸው አሁን ላይ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
አክለውም ማንኛውም የጤና እክል ቢያጋጥም እንኳን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በበኩሉ ይፋ ባደረገው ወቅታዊ ሪፖርት በአፋር ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለ6 ሺ 780 ቤተሰቦች የምግብ እርዳታ መድረሱን ገልጾ ይሁን እንጂ 2 ሺ 250 ቤተሰቦች ምንም አይነት ድጋፍ ሳያገኙ ቀርተዋል።” ብሏል።
በዚሁ መረጃ መሠረት የአደጋ አስተዳደር ኮሚሽን ወደ እነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች 16 ምግብ የጫኑ መኪናዎችን መላኩን አመልክቷል፤ በተጨማሪም ከዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም እና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ድጋፍ ይጠበቃል ብሏል።
ክልሉ ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ የሆኑት አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የነብስ አድን ምግቦችን በማቅረብ፤ በቋሚነት ውሃ የሚያመላልሱ ሁለት ቦቴ መኪኖችን በመመደብ፤ በመጠለያ ጣቢያዎች 15 ሮቶዎችን በማስቀመጥ እንዲሁም አልባሳትን በመስጠት ለተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አክለውም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበረሰቦችን ከአደጋ ቃጠና በማራቅ ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ በማስፈር፤ ውሃ በቦቴ መኪና በማቅረብ እና አከባቢዎችን በመጠበቅ “የህዝብ አለኝታነቱን” አስመስክሯል ብለዋል።
በአፋር ክልል በተለይ በአዋሽ እና ዱለቻ ወረዳ በሬክተር እስኬል 5.8 የደረሰ ተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ58 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
በተጨማሪም ከሰም ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ ከ30 በላይ መኖሪያ ቤቶች፣ 37 ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።
በክልሉ በገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳቶችን ያስከተሉ ትላልቅ አደጋዎች መደረሳቸውና የድርጅቱ ኃይል ማከፋፈያ ህንጻ መፍረሱም ተገልጿል። የኤሌክትሪካል እና መካኒካል ጉዳቶችም መደርሳቸውን የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አሊ ሁሴን ተናግረዋል፡፡
ከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳቶችን ያስከተሉ ትላልቅ አደጋዎች መደረሳቸውና የድርጅቱ ኃይል ማከፋፈያ ህንጻ መፍረሱ ተገልጿል። የኤሌክትሪካል እና መካኒካል ጉዳቶችም መደርሳቸውን የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አሊ ሁሴን ተናግረዋል፡፡
የከሰም ግድብ አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አቶ ቢኒያም ግድቡ የመሬት መንቀጥቀጥን እንዲቋቋም ታስቦ በትላልቅ አለቶች እና አሸዋ የተሰራ በመሆኑ በሬክተር ስኬል እስከ 7 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋም ግድብ መሆኑን ተናግረዋል።አስ