
አዲስ አበባ፣ ጥር 8/ 2016 ዓ/ም፡- የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የትግራይ ክልል ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የከለከሉ አምስት ትምህርት ቤቶች በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ አዘዘ።
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአክሱም ከተማ 159 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሃይማኖታዊ ልብሳቸው ምክንያት ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መታገዳቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶቹን ከሷል።
አቤቱታውን የተመለከተው የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የሚከለክለውን መመሪያ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ታግዶ እንዲቆይ ወስኗል።
በተጨማሪም መመሪያው በተማሪዎች ላይ “ሊመለስ የማይችል የመብት ጥሰት” ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል።
መመሪያውን አስተላልፈዋል የተባሉትን በከተማዋ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶችም ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ዶቼ ቬለ በዘገባው አመልክቷል።
በቅርቡ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ሙስሊም ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ለማከናወን “ሂጃብ እንዲያወልቁ” መጠየቃቸውን ባለመቀበላቸው ጥር 2 ቀን የተደረገው ምዝገባ እንዳለፋቸው መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ተማሪዎቹ “ሂጃባቸውን እስካላወለቁ ድረስ ምዝገባቸውን እንዲያጠናቅቁ ትምህርት ቤቶቹ መከልከላቸውን” ገልጸው ይህም የሃይማኖታዊ እምነትን መጣስ ነው ብለዋል።
በወቅቱ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ የሆኑት ሃጂ መሀመድ ካህሳይ ክልከላው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት እንዳይከታተሉ መከልከሉን ተከትሎ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “ጥያቄያችን በሦስት ቀናት ውስጥ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ከአማኙ ጋር በመመካከር ቀጣይ ሰላማዊ እርምጃ የምንወስድ ይሆናል” ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል። አስ