
አዲስ አበባ፣ ጥር 9/ 2017 ዓ/ም፦ አለምአቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆሪቋሪ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች በጎርጎሮሳውያኑ 2024 ኢትዮጵያ “መጠነ ሰፊ ግጭቶች እና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እገዳዎች” ማስተናገዷን በመጥቀስ የሰብዓዊ መብት ሁኔታውን “አስከፊ” ሲል ገልጾታል።
ድርጅቱ አዲስ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ግጭት ባለበት አካባቢዎች እና በሀገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች በመንግስት የጸጥታ አካላት፣ በሚሊሻዎች እና በታጣቂ ቡድኖች ከባድ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አመልክቷል።
በተለይም በአማራ ክልል ያለው ግጭት አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች “የጦር ወንጀል” ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።
ሂውማን ራይትስ ዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት መረጃን ዋቢ በማድረግ የመንግሥት የጸጥታ አካላት “ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ ማሰቃየት እና የሲቪል ዜጎች ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ” መፈጸማቸውን ጠቁሟል።
ለአብነትም ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከፍተኛ “የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ አካላት” በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ “በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ እንደገደሉ” አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም “የፋኖ ታጣቂዎች” በሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ በሲቪል ንብረቶች ላይ ጥቃት መሰንዘር እና ህገ-ወጥ እስራት በመፈጸም ተጠያቂ እንደነበሩ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጠቁሟል።
በክልሉ “ከፍተኛ የጥቃት ድርጊቶች የተመዘገቡበት” እንደሆነ ጠቅሶ በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።
በጎርጎሮሳውያኑ 2024 ስምንት የረድኤት ሰራተኞች የተገደሉ ሲሆን ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እየጨመረ የመጣውን አደጋ ተከትሎ የእርዳታ ስራዎቹን ለማስቆም እንዲያስብ አድርጎታል ተብሏል።
በተመሣሣይ በትግራይ ክልል አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች እንዲሁም የሲቪሎችን ንብረት መዝረፍ የመሳሰሉ ድርጊቶች “በኤርትራውያን ወታደሮች” ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተፈጸሙ የሚገኙ ጥሰቶች መሆናቸውን ጠቅሷል።
ሪፖርቱ በተጨማሪም በመላ አገሪቱ ሰዎችን ለገንዘብ ሲባል የማገት ተግባር መበራከቱን ጠቅሶ በተለይም በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ ከ100 በላይ ሰዎች መታገታቸውን አመልክቷል።
እንዲሁም ከየካቲት እስከ ሰኔ ወር በቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾችን ኢላማ ያደረጉ የጅምላ እስራት እና የእንቅስቃሴ ገደቦችን እንዲፈጸሙ ማመቻቸቱን ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች፣ የደህንነት ኃላፊዎች እና ምሁራንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች መታሰራቸውን መዝግቧል።
“ሚዲያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ሆነው ቀጥለዋል፤ ብዙ ጋዜጠኞችም ራሳቸውን ሳንሱር መደረግ አልያም በመታሰር ወይም በመሰደድ መካከል መምረጥ ነበረባቸው ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል። በዚህም ከጎርጎሮሳውያኑ 2020 ጀምሮ 54 ጋዜጠኞች ከአገሪቱ መሰደዳቸውን አመልክቷል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ከፍተኛ ጫና እንደተፈጠረባቸው ጠቅሶ ለአብነትም በግንቦት ወር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሰራተኞች “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” ጥቃት እንደደረሰባቸው አንስቷል።
እንዲሁም በህዳር ወር 2017 ዓ.ም መንግስት የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)ን ጨምሮ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማገዱ ተመላክቷል።
ተሟጋች ድርጅቱ አክሎም መንግስት በሚያዝያ ወር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መቀበሉን ገልፆ ነገር ግን ግልጽ እና ገለልተኛ የሆነ ቁጥጥር ባለመኖሩ ምክንያት “በቂ ያልሆነ” ሲል ተችቶታል።
በመቀጠልም “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት ውድቅ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል” ሲል ገልጿል።
በተጨማሪም “የኢትዮጵያ መንግሥት አለም አቀፍ አጋሮች እየተካሄዱ ያሉትን የመብት ጥሰቶች ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ከመንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመደበኛ ሁኔታ ቀጥለዋል” ብሏል። አስ