
አዲስ አበባ፣ ጥር 12/2017 ዓ.ም፡- በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት በክልሉ የተገኘችውን የሰላም ጭላጭል የሚያጨልም ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀጻጻስ የሆኑት አቡነ ማትያስ ለህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና ለግዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በተናጠል በጻፉት ደብዳቤ ገለጹ።
“ሁኔታዎች ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ፤ የተገኘችውን የሰላም ጭላጭል ሊያጠፋ ወደሚችል ሁኔታ እያመራ ይገኛል፤ ይህንን እያየን ዝምታን መምረጥ በሰውና በፈጣሪ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ይህንን የምክር ደብዳቤ ለመጻፍ ተገድጃለሁ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀጻጻስ የሆኑት አቡነ ማትያስ በደብዳቤያቸው ሁለቱን አመራሮች በአካል አግኝተው ለመወያየት ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸው በመጠቆም ደብዳቤውን ለመጻፈ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም “ሁኔታው ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ፣ ልዩነቶቻችሁ እየሰፉ፣ ያልተለመደ አካሄድ እየተዘወተረ፣ በስነስርአት መወያየት ቀርቶ መዘነጣጠል እየሰፋ በመሄድ ላይ በመሆኑ እና ህሊናየ እረፍ በማጣቱ ነው” ደብዳቤውን ለመጻፍ የተገደድኩት ብለዋል
በትግራይ የተፈጸመው በደል እጅግ አሳዛኝ እና ከባድ ነው ሲሉ በደብዳቤያቸው የገለጹት አቡነ ማትያስ የፕሪቶርያው ስምምነት ከጦርነቱ የተረፈውን የክልሉን ህዝብ ወደ መደበኛ ህይወቱ ይመልሰዋል በሚል ተስፋ አድርገው እንደነበር ጠቁመዋል።
በአመራሩ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት እንኳን የትግራይ ህዝብ የተቀረው የአለም ህዝብ ያላሰበው ነው ሲሉ በአመራሩ መካከል የተፈጠረው ልዩነት እጅግ አስደንጋጭ ነው ሲሉ የገለጹት ፓትርያርኩ ችግራችሁን በመወያየት ትፈቱታላችሁ ብለን ብንጠብቅም አልሆነም ሲሉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
“ትልልቆች እና አሳቢዎች በመሆናችሁ እንዲሁም የህዝባችሁን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት እራሳችሁ ተወያይታችሁ ትፈቱታላችሁ ብለን ጠብቀን ነበር” ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ችግር በተዳረገበት ወቅት እንዴት ህዝባችሁን እረስታችሁ ወደዚህ አይነቱ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ገባችሁ ሲሉ ሀዘናቸውን የገለጹት ፓትርያርኩ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በጭፍጨፋ በርካታ የክልሉ ህዝብ መጎዳቱን አመራሮቹ ራሳቸው በመርዶ አዋጅ መግለጻቸውን አስታውሰዋል፤ “ለዚህ ህዝብ ካሳው ይህ ነውን” ሲሉ ጠይቀዋል።
በእልክ እኔ እሻላለሁ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን እኔ ብቻ ነኝ ለህዝብ የማስበው በሚል በተፈጠረው ውስብስብ ችግር የሚያዝን እንጂ የሚደሰት ህዝብ የለም ሲሉ ጠቁመዋል።
በአመራሩ መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዳይበቃ በአንድነት ተስማምቶ ሲኖር በነበረው ህዝብ መካከልም እየወረደ ይገኛል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
አላማችሁ ህዝብ ማገልገል ከሆነ እየሄዳችሁበት ያለው አካየድ የጥፋት አካየድ በመሆኑ ለህዝባችሁ ስትሉ ሰከን ብላችሁ አስቡ ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ይህን የማታደርጉ ከሆነ ግን እየሄዳችሁበት ያለው አካሄድ ሁሉንም የሚያጠፋ፣ የተገኘችውን ሰላምም የሚረብሽ በመሆኑ ህዝባችሁ የሚሰጣችሁን ምክር ተቀብላችሁ የህዝባችሁን ጥያቄ እንድትመልሱ አደራ እላለሁ ብለዋል።
ከሳምንት በፊት የኦሮሚያና አማራ ክልል እንዲሁም በሀገሪቱ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች ቆመው ነዋሪዎች ሰላምን እንዲያገኙ፤ በትግራይ ክልል ያለው የአስተዳዳሪዎች አለመግባባት ተፈቶ ዕረፍት ያጣው ሕዝብ መረጋጋት እንዲችል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ፓትርያርኩ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ባስተላለፉት የሰላም ጥሪ የሰላም ትርጉሙ ተረጋግቶ መኖር፣ ወደ ዓላማ ፍጻሜ መድረስ፣ መርቆ ማለፍ ነው፤ ካሉ በኋላ “ወልዶ ለመሳም፣ አሳድጎ ለመዳር፣ ዐርፍተ ዘመን የጌታቸውን በክብር ለመሸኘት ሰላም አስፈላጊ ነው” ብለዋል። አስ