
አዲስ አበባ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም፦ በአፋር እና በኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች መከሰታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፤ “በአዋሽ እና ዱሌቻ ወረዳዎች ያሉ የተወሰኑ ነዋሪዎች በተለይም ከብቶቻቸው እና ንብረታቸው ላይ ስጋት ያላቸው የአርብቶአድር ማህበረሰቦች ወደ ሌላ ቦታ ለመዘዋወር ፈቃደኞች አይደሉም” ሲል ገልጸ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት መሠረት፤ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አደጋ ካለባቸው አካባቢዎች ለማስወጣት አስገዳጅ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበ ነው።
ከአያኤኤሲ ክላስተር አስተባባሪዎች እና አጋሮች ድጋፍ በተዘጋጀው አዲስ መረጃ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፤ በኦሮሚያ ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰቱ ባሉበት አካባቢዎች የፀጥታ ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
“400,000 የሚጠጉ ከብቶች የተዘዋወሩበት ቦታዎች እንስሳቶቹን ለማቆየት ተስማሚ መሬት የሌለው በመሆኑ የአርብቶ አደሮችን ኑሮ በእጅጉ አስተጓጉሏል” ሲልም አክሏል። በተጨማሪም “በግብርና አርብቶ አደር ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበረሰቦች ከፍተኛ ፈተናዎችን እየገጠማቸው ነው፤ ከእነዚህም መካከል ሰብሎችን መተው፣ ለተፈናቀሉ ከብቶች የሚሆን መኖና ውሃ እጥረት፣ በዚያ ከነበሩ ማህበረሰቦች ጋር የሚደረግ ፉክክር እንዲሁም በከብት እንስሳት መካከል በሽታ የመስፋፋት ስጋት ይገኙበታል” ብሏል።
እንደ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ገለፃ ቀጣይነት ያለው ወደ ሌላ ማዘዋውር እና አዳዲስ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መምጣት በአስቸኳይ በቂ መጠለያ የማግኘት ፍላጎትን አባብሷል።
“ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ እንደ ፕላስቲክ ጣሪያ ወይም በጥሩ ሁኔታ ባልተገነቡ ባህላዊ በሆኑ በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እየኖሩ ሲሆን፣ ይህም በቀል ለከባድ ሙቀት፣ በምሽት ለቅዝቃዜ እና ለከባድ ነፋስ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል” ሲል በአፅንዖት የገለጸው ድርጅቱ፤ “የአጎበር እጥረት የወባ ወረርሽኝ አደጋን የሚጨምር ሲሆን የተገቢ መጠለያ አለመኖር በተለይ የሴቶች እና የህፃናት ተጋላጭነትን ይጨምራል” ብሏል።
ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ ስታንዳርድ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ተከትሎ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በተጨናነቀ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የውሃ፣ ምግብ እናሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን ዘግቧል። በርካታ ነዋሪዎች ከመንግስትና ከሰብአዊ ድርጅቶች የሚገኘው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፤ በዚህም ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በአፋር ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለ6 ሺ 780 ቤተሰቦች የምግብ እርዳታ መድረሱን ገልጿል። ይሁን እንጂ 2 ሺ 250 ቤተሰቦች ምንም አይነት ድጋፍ ሳያገኙ ቀርተዋል ብሏል። አስ