
አዲስ አበባ፣ ጥር 13/2017 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ አጠቃላይ የመንግስት የውጭ እና የሀገር ውስጥ የዕዳ መጠን ባለፉት አምስት አመታት ብቻ 25 ነጥብ 3 በመቶ መጨመሩ ተጠቆመ፤ መንግስት ማስተማመኛ የሰጠባቸው (guaranteed debt) እና ማስተማመኛ ያልሰጠባቸው (non-guaranteed debt) ዕዳዎችን ጨምሮ የሀገሪቱ አጠቃላይ የዕዳ መጠን 68 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መድረሱ ተገልጿል።
እስከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 መጨረሻ ድረስ የዕዳ መጠኑ የሀገሪቱን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 32 ነጥብ 9 መሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል።
በሪፖርቱ ለዕዳ መጠኑ መጨመር በዋናነት የተጠቀሰው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ መጠን መዋዠቅ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም ባለፉት አምስት አመታት ዋነኛ ነበር ብሏል።
ከአጠቃላይ የዕዳ መጠኑ ውስጥ 59 በመቶ ወይንም 40 ቢሊየን ዶላሩ ከሀገር ውስጥ አበዳሪዎች የተገኘ መሆኑን የጠቆመው የገንዘብ ሚኒስቴሪ ሪፖርት ቀሪው 41 በመቶ ወይንም 28 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ከውጭ አበዳሪዎች የተገኘ ነው ብሏል።
ባለፉት አምስት አመታት የሀገር ውስጥ ዕዳ በ14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ያለው ሪፖርቱ የውጭ ዕዳ ደግሞ 2 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ነው እድገት ያሳየው ሲል አስታውቋል።
የውጭ ብድር ክምችት ዝቅተኛው ጭማሪ እንዲያስመዘግብ ያደረገው የዶላር የውጭ ምንዛሬ መጠን መዋዠቅ እና ዝቅተኛ የውጭ ብድር ክፍያ ናቸው ሲል በምክንያት አስቀምጧል።
ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ውስጥ ከፍተኛ መጠኑ በረዝም አመት ክፍያ እና በእፎይታ ግዜ ብድር ከሚሰጡ ከአለም አቀፍ ኤጀንሲዎች የተገኘ መሆኑን እና ይህም 52 በመቶ የሚሆነው እንደሚይዝ ሪፖርቱ አመላክቷል፤ በሁለትዮሽ በተደረገ ስምምነት ከአበዳሪዎች የተገኘው ደግሞ 28 ነጥብ 31 በመቶ ድርሻ አለው ብሏል። የተቀረው ደግሞ ከግል አበዳሪዎች የተገኘ ዕዳ ነው ሲል ገልጿል።
የአሜሪካ ዶላር የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ክምችት 45 ነጥብ 84 በመቶ የሚሆነውን ሸፍኗል ያለው ሪፖርቱ ዩሮ 6 ነጥብ 58 በመቶ እና የቻይና ዩዋን ደግሞ አንድ ነጥብ 52 በመቶ በመሸፈን ይከተላሉ ብሏል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው ሪፖርቱ የሀገሪቱ እዳ በአለም አቀፍ ተቋማት መመዘኛ መሰረት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል አስተባብሏል፤ በአለም ባንክ እና በአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) መነሻ መስፈርት መሰረት የሀገራት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከ35 በመቶ መብለጥ የለበት እንደሚል አመላክቷል። የዕዳ መጠኑ የሀገሪቱን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 32 ነጥብ 9 መሆኑን ጠቁሟል። አስ