ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: በአክሱም ትምህርት ቤቶች የተደረገውን የሂጃብ እገዳን በመቃወም በመቀለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታደሙበት ሰልፍ ተካሄደ

ሰልፈኞቹ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲከበር ጠይቀዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 13/ 2017፦ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የታደሙበት ሰልፍ ዛሬ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ ተካሄደ።

ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሂጃብ ለመልበስ የሚያስችላቸውን መብት ያረጋግጣሉ የተባሉትን የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ መመሪያዎችን በመተግበር ረገድ እየታዩ ናቸው ያሏቸውን መለሳለስ በመቃወም ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በትግራይ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተዘጋጀው ሰልፉ፤ “ሂጃቧንም ትለብሳለች ትምህርቷንም ትማራለች” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ ሮማናት አደባባይ ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ አደም አብዱልቃድር በበኩላቸው “ሴት ልጆቻችን ከፍርድ ቤት እና ከትምህርት ቢሮው በግልጽ የተላለፉ መመሪያዎችንና ውሳኔዎች ቢኖሩም አሁንም ትምህርት እንዳይከታተሉ እየተከለከሉ ነው” ብለዋል።

አክለውም “በክልሉ እስልምና ለብዙ መቶ ዘመናት የባህል አካል በሆነበት ሁኔታ ይህ በጣም የሚያሳስብ ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።

አያይዘውም ሰላማዊ ሰልፉ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ጋር በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን “ችግሩ ሳይፈታ ቀርቶ ሴት ልጆቻችንም ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ አሁንም እየተከለከሉ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም “ከአንድ አመት በፊት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው ከህዝባቸው ጋር በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል፣ አሁን ደግሞ ሂጃባቸውን ለብሰው ትምህርታቸውን መማር ይገባቸዋል” ብለዋል።

እንዲሁም “ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ገልጸዋል፣ እኛም ይህን ሰልፍ በተረጋጋና አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ እየመራን ነው” ሲሉ የሰልፉን ሰላማዊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ተቃውሞው የተፈጠረው በአክሱም ከተማ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ በመልበሳቸው ምክንያት በወሩ መጀመሪያ ላይ ለብሔራዊ ፈተና  እንዳይመዘገቡ መደረጋቸውን ጨምሮ ለወራት የዘለቀውን እልባት ያልተገኘለት ቅሬታ ተከትሎ ነው።

ተማሪዎቹ የትምህርት ቤት ሃላፊዎች ሂጃባቸውን እንዲያወልቁ መገደዳቸውን ተከትሎ በሕገ መንግሥቱ በተረጋገጠው የሃይማኖት ነፃነት መሠረት መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን በመጥቀስ ተቃውመዋል።

በዚህም ምክንያት ወደ 160 የሚጠጉ ሙስሊም ተማሪዎች የምዝገባ ቀነ ገደብ አልፏቸዋል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የአክሱም ከተማ ፍርድ ቤት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን መመሪያ ማገዱ ይታወሳል። በተጨማሪም አምስት ትምህርት ቤቶች በተከሰሱበት ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠርተዋል።

ዛሬ ጥር 13 በተካሄደው ሰላማዊው ሰልፍ ላይ የተሳተፉት ጠበቃ ሙስጠፋ አብዱ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት የሰልፉ ዋና አላማ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ከእምነታቸው እና ከትምህርታቸው መካከል እንዲመርጡ የሚያስገድድ ምንም አይነት ህጋዊ መሠረት የለም” ያሉት የሕግ ባለሙያው አክለውም “ሂጃባቸውን ለብሰው ትምህርት ቤት የመማር መብት አላቸው ለዚህም ነው ተቃውሞ እያሰማን ያለነው” ብለዋል።

ጠበቃ ሙስጠፋ አብዱ ሂጃብ መልበስ ለብዙ ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ ገልጸው ይህም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን ጨምሮ በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ማዕቀፎች ስር ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን አስረድተዋል።

“በየትኛውም ሀይማኖት ላይ ተቃውሞ እያደረግን አይደለም፣ ነገር ግን የክልሉ መንግስት ህግን እንዲያከብር እና ተማሪዎች መብታቸው በሚፈቅደው መሰረት እንዲማሩ እንጠይቃለን” ብለዋል።

የ65 ዓመቱ ሰልፈኛ አብዱራህማን ቢላል በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት “ሂጃብ መልበስ የሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታዊ ግዴታ በመሆኑ በሃይማኖት ክርስቲያን የሆኑ ወገኖች ሳይቀሩ ክልከላውን እያወገዙ ነው” ብለዋል።

አክለውም “ውሳኔው እንዲከበርልን እና ሴት ልጆቻችን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እንጠይቃለን” ብለዋል።

ሌላዋ የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ ሪሃማ ሰኢድ በበኩሏ የትምህርት ቤቶቹን ድርጊት “ህገወጥ” ስትል ገልጻዋለች።

“ፍርድ ቤቱ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ውሳኔያቸውን አስተላልፈዋል ነገር ግን ትምህርት ቤቶቹ ችላ ብለውታል” በማለት ገልጻለች።

“እነዚህን ውሳኔዎች ለማስፈጸም ምንም የተደረገ ነገር ባለመኖሩ፣ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለስልጣናት እርምጃ እንዲወስዱ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተገደናል” ብላለች።

የክልሉ እስልምና ማህበረሰብ ተወካዮችም ሰልፉን ተከትሎ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ጋር ​​በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በዚህም “ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆን የለባቸውም” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ሂጃብ የለበሱ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መገለል እንደሌለባቸው የመንግስታቸውን አቋም አረጋግጠዋል ሲል ድምጺ ወያነ ዘግቧል።

“እንደ መንግሥት ሕገ መንግስታችን ግልጽ ነው።” በማለት ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳው ሰላማዊና ስርዓት ያለው ጥያቄ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሴት ሙስሊም ተማሪዎች በሂጃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሊስተጓጎሉ አይገባም፤ እንደ መንግስት

ለረጅም ጊዜ ተከባብረውና ተግባብተው የኖሩ ህዝቦች አሁን ላይ ወደ ግጭት የሚያመሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ቶሎ መታረም ያለበት እና ስሜታዊ መሆን እንደማያስፈልግ ገልጸዋል።

ከእኛ አቅም በላይ ባለመሆኑ ከውጭ ሀይል የሚመጣ ድጋፍ አያስፈልገንም ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button