
አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱ በድጎማ የተሰጠውን 13 ቢሊየን ብር ለታለመለት አላማ ማዋሉን ለማረጋገጥ የመስክ ምልከታ እያደረኩ ነው ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
ለክልሉ ለ2017 በጀት አመት የተሰጠው ድጎማ የስድስት ወር እቅድ አፈፃፀም ለመመልከት እና ድጎማው ለታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጥ የመስክ ጉብኝቱ ዋነኛ አላማ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በድጎማ የሚሰጠው በጀት አተገባበር፣ ውጤታማነት እና አጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱ ምን ይመስላል የሚለው በመስክ ምልከታው ትኩረት የሚደርግባቸው መሆኑን ምክትል ሰብሳቢው መናገራቸውን ምክርቤቱ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።
የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ የስራ ክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወራት ሪፖርት ማቅረባቸውንም ጠቁሟል።
የክልሉ የኢኮኖሚ ቢሮ ሃላፊዎች “ለሰሜኑ ጦርነት ለተጎዱ መቋቋሚያ የተመደበው 20 ቢሊዮን ብር እስካሁን አልተለቀቀም” ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያመላከተው የምክር ቤቱ መረጃ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ በሰጡት ምላሽ “ለሰሜኑ ጦርነት ለተጎዱ መቋቋሚያ የተመደበው 20 ቢሊዮን ብር ሶስት ጊዜ መፅደቁን አስታውሰው ገንዘቡ ተለቆ” የህዝቡን ችግር መፍታት አለበት ማለታቸውንም አካቷል።
በተጨማሪም ሃላፊዎቹ “የበጀት ድልድል ቀመር ጉዳይ ወቅቱን ያገናዘበ አለመሆኑን” ገልጸዋል ያለው መረጃው የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ በሰጡት ምላሽ “የበጀት ቀመርን በሚመለከት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የሚመለከት ጉዳይ ቢሆንም በትኩረት የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል” ብሏል።
ከከተማና ገጠር ሴፍትኔት፣ ከፕሮጀክቶች ጋር በተገናኘ፣ ከፌደራል በሚመደበውና ከውጭ በእርዳታ በሚገኘው የባለ ብዙ ዘርፍ የበጀት ጉዳይን በተመለከተ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የክልሉ ሃላፊዎች በዝርዝር ማቅረባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል።
በተጨማሪም የ 17 ወራት የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ አለመከፈሉ ሰራተኛውን አስተባብሮ ለማሰራት ፈተና እንደሆነባቸው፣ ከማህበራዊ ዋስትና ጋር በተያያዘ እድሜያቸው ለጡረታ የደረሱ ሰዎች የ 17 ወራት ካልተከፈለ ጡረታ መውጣት አይቻልም በመባሉ ሰዎች ለችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) ሴፍትኔትን በተመለከተም የቀረበው ሪፖርት አፈፃፀሙ መልካም መሆኑን፣ ከበጀት አጠቃቀም ጋር ያለው ግልፀኝነት የሚበረታታ ነው ማለታቸውንም መረጃው አመላክቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ ምህረት በየነ (ዶ/ር) ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የቋሚ ኮሚቴው እገዛ ያስፈልገናል ማለታቸውም ተገልጿል።