
አዲስ አበባ፣ ጥር 14/ 2017 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በፍርድ ቤት ዳኞች ላይ በተፈጸመ ድብደባ እና ዛቻ ምክንያት የወረዳው ፍርድ ቤት አገልግሎት መስጠት ማቆሙን የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ገለፁ።
ድብደባ እና ዛቻው ጄኔኑስ ነጋሳ እና ቀነኒሳ ከበበው የተባሉ ዳኞች ላይ መፈጸሙን የተገለጸ ሲሆን በተለይ ጄኔኑስ ወደ ወታደራዊ ካምፕ ተወስደው ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያው “ስድስት ሰዎች ሆነው መሬት ላይ ጥለውኝ የቻሉትን ያህል መላ ሰውነቴን ራጋገጡን። በብረት ቀበቶ ፊቴን ሲገርፉኝም ነበር። ትንፋሽ ሲያጥረኝ አንስተው ወደ ክፍል መለሱኝ” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የህግ ባለሙያ ቀነኒሳ በቁጥጥር ስር የዋሉትን የስራ ባልደረባቸውን ጉዳይ ከባለስልጣናት እና ከአዛዦቹ ጋር ከተነጋገሩ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል። አክለውም የወረዳው አስተዳዳሪ መሃል በመግባታቸው ከድብደባ መትረፋቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎም የህግ ባለሙያዎቹ ወረዳውን ለቀው በመውጣታቸው፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት በሁለቱ ባለሙያዎች ብቻ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የያያ ጉለሌ ወረዳ ፍርድ ቤት አገልግሎት ተቋርጧል ሲሉ የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዘነበ ነጋሽ ተናግረዋል።
በህግ ባለሙያዎቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት የህግ ባለሙያዎችን መብት የጣሰ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ጉዳዩ ላይ ከወረዳው ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ ነው ይህንን ወንጀል የፈጸሙ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ የፍርድ ቤት ዳኛ በሆኑት ጄኔኑስ ነጋሳ ላይ የተፈጸመውን ድብደባ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የያያ ጉለሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ መደብደባቸውን ካረጋገጠ በኋላ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በክልል ደረጃ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ገልጿል። በተጨማሪም ከተፈጸመው ድርጊት ጋር በተያያዘ ምርመራ እንዲደረግ ለዞኑ መመሪያ ተላልፎ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። አክሎም ምርመራው ሲጠናቀቅ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደግ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል።አስ