
አዲስ አበባ፣ ጥር 15/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወደ 10,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች በአዋሽ ፈናታሌ በተደጋጋሚ በደረሰው መሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት መፈናቀላቸውን አለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን (IFRC) ገለጸ።
እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ መክንያትም በአፋር ክልል 60 ሺህ ሰዎች እና በኦሮሚያ ክልል 20 ሺህ ሰዎች፣ በአማራ 10 ሺህ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በአጠቃላይ በሶስቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 100 ሺህ ገደማ ደርሷል።
የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን (IFRC) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበር፣ ኤፍራታ ግድም እና ሀገረማርያምን ጨምሮ ከ38 በላይ ወረዳዎች በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
“በአጠቃላይ 2,139 አባዋራዎች (9,995 ሰዎች) በቀጥታ ተጎድተዋል እንዲሁም ተፈናቅለዋል” ሲል ፌዴሬሽኑ ገልጿል። አክሎም “ከ 360 በላይ መኖሪያ ቤቶች ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን 908 ሄክታር የእርሻ መሬት እና 23 ኪሎ ሜትር መንገድ ላይም ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
ከመስከረም 2016 መጨረሻ ጀምሮ የአፋር፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን የሚሸፍነው ዋናው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ በተከታታይ እና ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥና ንዝረት አስተናግዷል። የዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከል የሆነው የፌንታሌ እሳተ ገሞራ ከ2013 ጀምሮ ቀስ በቀስ የመሬት አቀማመጥ ቅርጽ መቀያያር ምልክቶች አሳይቷል።
ባሳለፍነው መርም ከ20 በላይ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ የተከሰተ ሲሆን ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ በሬክተር እስኬል 5.8 የሆነ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ዶፋን ተራራ አቅራቢያ ተከስቷል።
የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን በአፋር ክልል ወደ 60,000 የሚጠጉ ሰዎች በቅርቡ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ተጎድተዋል ብሏል። ከእነዚህ ውስጥ ከአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ 25,000 እና ከዱለቻ ወረዳ 15,000 የሚሆኑትን ጨምሮ 40,000 ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርጓል።
በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ በሰባት ቀበሌዎች ወደ 27,120 የሚጠጉ ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጡ ተጎድተዋል ያለው ድርጅቱ 20,720 ግለሰቦች ወደ 11 መደበኛ ያልሆኑ የተፈናቃይ ጣቢያዎች ተዘዋውረዋል ብሏል። እነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ አደጋ ካጋጠማቸው አካባቢዎች ርቀው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን ያካትታሉ ሲልም አክሏል።
ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ ስታንዳርድ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ተከትሎ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በተጨናነቀ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የውሃ፣ ምግብ እናሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን ዘግቧል። በርካታ ነዋሪዎች ከመንግስትና ከሰብአዊ ድርጅቶች የሚገኘው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፤ በዚህም ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተያዘው ሳምንትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአፋር ክልል በርዕደ መሬት የተጎዱ ዜጎችን የጎበኘ ሲሆን ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን ገልጿል።አስ