ዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበርና ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በበርካታ ከተሞች አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15/ 2017 ዓ/ም፡- በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እና ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉ በርካታ ከተሞች ዛሬ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄዱ።

ሰልፎቹ በአድዋ፣ አክሱም፣ ሽሬ፣ አቢ አዲ፣ አዲግራት፣ ሽራሮ፣ ላላይ ኮራሮ፣ እንዳባጉና፣ አዲ ዳዬሮ፣ ሰለክላካ እና ኔቤልትን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ተደርገዋል።

የአዲግራት ከተማ ተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት ብርሃኔ ካህሣይ፤  “የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ በአዲግራት ብቻ 27 ህፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ290 በላይ ተፈናቃዮች በረሃብ እና በበሽታ ምክንያት ሞተዋል” ብለዋል። 

አክለውም “መከራውን መቋቋም የማይቻል ከባድ ነው፣ እናም ዛሬ ለህዝባችን እርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ ድምፃችንን ከፍ እናሰማለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

እንደ አቶ ብርሃኔ ገለፃ በአዲግራት ከተማ ብቻ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች በሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል።

አክለውም “ሁሉም ወገኖች በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ከፍተኛ ስቃይ እንዲገነዘቡ እና ወደ ቤታቸው የመመለሳቸውን ሂደት እንዲያፋጥኑ እንጠይቃለን” ብለዋል።

ሌላኛው በአድዋ ከተማ የተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት ዴዚኔት በበኩላቸው ተመሳሳይ ስጋትን ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“በዛሬው ሰልፍ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል” ያሉት አስተባባሪው ” ያለ በቂ እርዳታ እና የሕክምና ድጋፍ እየተቸገሩ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን” ብለዋል።

አክለውም “ለድጋፋችሁ ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን” ሲሉ ገልጸው “በቀዬአችን ያለ ምንም ሁከት ስጋት በሰላም የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን እንጠይቃለን” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች “የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መተግበር አለበት”፤ “በቀዬአችን የመኖር መብታችን መጠበቅ አለበት” እና “ያለ እርዳታ እየሞትን ነው” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው አብረኽት ግደይ በበኩሏ የተጠየቁት ነገሮች አስቸኳይ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥታ ተናግራለች።

በተጨማሪም “ወደ ቤታችን የመመለስ መብትን ለመጠየቅ ነው የተሰባሰብነው፣ ከእንግዲህ ያለእርዳታ በድንኳን ውስጥ መኖር አንችልም” ብላለች።

እነዚህ ሰልፎች የተከናወኑት “ጽላል ለምዕራብ ትግራይ” በተሰኘ የሲቪል ማህበረስ ድርጅት አዘጋጅነት ባሳለፍነው ሳምንት በመቀሌ ከተማ ለሶስት ቀናት የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ ነው። ተፈናቃዮቹ በተላየዩ መንገዶች ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን በሰልፉ ላይ ሲያሰሟቸው ከነበሩ መልዕክቶች መካከል “ወደቀያችን መልሱን”፣ “በኬንዳ መጠለያ መኖር ይብቃን”፣ “ትኩረት በሱዳን ለሚገኙ ስደተኞች” የሚሉት ይገኙባቸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button