
አዲስ አበባ፣ ጥር 26/ 2017 ዓ/ም፦ የጅቡቲ መከላከያ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ድንበር በስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጅቡቲዋ አዶርታ ከተማ ጥር 22 ቀን የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አረጋገጠ። በጥቃቱ “ስምንት አሸባሪዎች” እንደተገደሉ እና ንጹሃን ዜጎችም መገደላቸውን ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ቅዳሜ ጥር 24/ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ ቦታው “ለአንድ ሳምንት ያህል በክትትል ስር” እንደነበረ እና በቡድኑ ጥቅም ላይ የዋለ “የሎጂስቲክስ እና የዘመቻ ቤዝ” እንደሆነ ተለይቷል ብሏል።
ሚኒስቴሩ ጂቡቲ ሲቪሎችን ጭምር ያካተተ “ሞት” መከሰቱን በመግለጽ በቦታው ስለመገኘታቸው ሁኔታ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል። ለተጎዱ ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ እንደተላከላቸውም አክሏል።
ዒላማ የተደረገው ቡድን “በሦስት የተለያዩ መንገዶች ዘልቆ መግባትን ጨምሮ በግጭት ድርጊቶች ላይ ተሰማርቷል” በማለት ገልጿል። ይህም “በወታደሮች ለተያዙ ቦታዎች እና ለአሳል ሀይቅ ስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማት ስጋት ሊሆን ይችላል” ብሏል። በተጨማሪም ቡድኑ “በገጠር ትምህርት ቤት መምህራን ላይ እገታ በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ” እና “የአሳል ሐይቅ-ታጁራ ኮሪደርን አደጋ ላይ እንደጣለ” ገልጿል።
መግለጫው የወጠው በአፋር ክልል በኢትዮ-ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኤሊዳዓር ወረዳ ሲያሩ ቀበሌ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ነዋሪ፤ ጥቃቱ ሌሊት ላይ በተከታታይ መፈጸሙን ገልጸው በጥቃቱ ነፍሰ ጡር ሴት እና ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ “ከስምንት በላይ ሰዎች መገደላቸውን” ገልጸዋል። በተጨማሪም ቢያንስ አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ሁለቱ በዱብቲ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው ነዋሪ “ድሮኖች አካባቢውን ዒላማ ሲያደርጉት በሁለት ወራት ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ ነው” መሆኑን እና ጥቃቱ የተፈፀመው የጅቡቲ መንግስት ተቃዋሚ በሆነው እና ራሱን አንድነትና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግምባር (FRUD) ብሎ የሚጠራው ቡድንን ለማጥቃት በሚል መሆኑን ገልጿል።
በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የጂቡቲ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ (LDDH) የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት በበኩሉ “አራት ሴቶችን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውን” እና “ሴቶችን እና ህጻናትን” ጨምሮ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን በመግለጽ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ “ሌሊቱን ሙሉ የአርብቶ አደሮች ካምፖችን በቦምብ ማጋየታቸውን ቀጥለዋል” ብሏል። ድርጅቱ ጥቃቱን “በአፋር ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ የጦር ወንጀል” ነው ሲል ገልጾታል።
የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም። አስ