
አዲስ አበባ፣ ጥር 26/2017 ዓ.ም፡- የጁቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ የሱፍ በካይሮ ጉብኝት ማካሄዳቸው ተገለጸ፤ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌን መልዕክት ለግበጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ማስረከባቸውም ታውቋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ የሱፍ ከግብጹ አቻቸው ጋር መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን ከውይይታቸው በኋላ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሀገራቸውን ወደቦችን ከጂቡቲ ወደቦች ጋር ለማስተሳሰር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።
የጁቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር በሀገራቱ ግንኙነት እና ትብብር ዙሪያም መምከራቸውን የግብጽ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አመላክተዋል።
በተጨማሪም አልሲሲ በአፍሪካ ቀንደ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ከጂቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋረ መምከራቸውን ያስታወቁት ቃል አቀባዩ በዋናነት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ በተለይም በሶማሊያ ያለውን ፀጥታና መረጋጋት ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።
አልሲሲ “የሶማሊያን ሰላም ጸጥታ እና ግዛታዊ አንድነት ለመደገፍ ግብጽ እንደምተሰራ” ለጂቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አረጋግጠውላቸዋል ብለዋል።
በቀይ ባህር ዙሪያም መወያየታቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ የቀይ ባህርን መደበኛ የባህር ጉዞን ለማስቀጠል፣ የባብ-ኤል-ማንደብ ሰርጥን ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲሉ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የጂቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒትር ማህሙድ አሊ የሱፍ ከግብጹ አቻቸው ባድር አብደላቲ ጋር መወያየታቸውን ከደይሊ ኒውስ ኢጂብት ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
“የግብጽ ወደቦችን ከጂቡቲ ወደቦች ጋር ለማስተሳሰር ተወያየተናል “ ሲሉ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ አስታውቀዋል።
ሁለቱ ባለስለጣናት ከውይይታቸው በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “የግብፅ ወደቦችን ከጅቡቲ ጋር ለማስተሳሰር እና በሎጂስቲክስ ዘርፍ ትብብር ለማድረግ ለሁለቱም ሀገራት ያለውን ትልቅ ጠቀሜታ ተወያይተናል” ማለታቸውን ዘገባው አካቷል።
ጅቡቲ በቀይ ባህር ላይ የተፈጠረው ቀውስ ተጋላጭነቷን እንዳባባሰው በመጥቀስ “የቀይ ባህርን ደህንነት እና የመርከብ እንቅስቃሴን ሰላማዊነት የማረጋገጥ የጋራ ግብ አለን” ማለታቸውም ተመላክቷል።
የጂቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱፍ በበኩላቸው የሀገራቱ “የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ልዩ ነው” ሲሉ በማወደስ “በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ እየታዩ ያሉ ለውጦች ቀጣይነት ያለው ምክክር እንደሚያስፈልግ አመላካች ናቸው ማለታቸውን ዘገባው አስታውቋል።
“እኛ በቀይ ባህር ደቡባዊ ግርጌ ላይ ስለምንገኝ እና ግብጽ ደግሞ በቀይባህረ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ መገኘቷ የግብፅ እና የጅቡቲ ብሔራዊ ደህንነት በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው ብለን እናምናለን” ማለታቸውንም አካቷል።
ሁለቱም ሚኒስትሮች በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሶማሊያ ጉዳይ ተወያይተዋል ያለው ዘገባው የሶማሊያ መንግስት እያካሄደው ያለውን የጸረ-ሽብርተኝነት ጥረቶች እና የማረጋጋት ስራ በቀጣይ በሀገሪቱ በሚሰፍረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ስር በሚሰፍረው ጦራቸው አመካኝነት ለማጎልበት መስማማታቸውንም ዘገባው አመላክቷል። አስ