
አዲስ አበባ፣ ጥር 30/ 2017 ዓ/ም፦ እነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው የክስ መዝገብ ሥር የሽብር ወንጀል ክስ ከቀረበባቸው 51 ተከሳሾች መካከል ትናንት ሐሙስ ፍርድ ቤት የቀረቡ 16 ተከሳሾች ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ “አልፈጸምንም” በማለት ተከራከሩ።
ተከሳሾቹ ተናንት ሐሙስ ጥር 29/2017 ዓ.ም. በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃል ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግም በተከሳሾች ተፈጽሟል ባለው ወንጀል ላይ ፍርድ ቤት አሻሽለህ ቅረብ ሲል ያዘዘውን የክስ መዝገብ አሻሽሎ አቅርቧል።
ተከሰሾች ተሻሽሎ በቀረበው የክስ መዝገብ ላይ ከ 1,100 በላይ ሰዎች ሞተዋል የሚለው ከእነ ስም ዝርዝራቸው፣ የተጎዱ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም እንዲሁ፣ እና በዚህ የወንጀል ድርጊት በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል የሚለው ተካቶ ቀርቧል ሲሉ ከተከሳሽ ጠበቆች መካከል አንደኛው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸን ጠቅሶ ዶቼ ቬለ ዘግቧል።
ችሎቱም ትከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ስለመፈፀም አለመፈፀማቸው የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ አድርጓል። በመጀመርያ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሃንስ ቧያሌው “የሽብር ቡድን አመራር በመሆን፣ አባል በመሆን፣ በማደራጀት፣ ስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት እና ጽንፈኛ የሆነውን ፋኖን በመምራት የሽብር ወንጀል ፈጽሟል” የሚሉት ክሶች “በፈጠራ የተሞሉ ናቸው”፣ “መረጃ አልባና ከእውነት የራቀም ነው” ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
“የፍትሕ ሚኒስቴር በእኔ እና በእኔ ስም በሚጠራው መዝገብ ላይ ያቀረበው ክስ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፤
አቶ ዮሐንስ አክለውም “ሕግን በመተላለፍ እና ወንጀል በመፈጸማቸው ሳይሆን ንቁ አማራዎች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራን” በመሆናቸው ምክንያት እንደተከሰሱ ለፍርድ ቤቱ መግለጸቻውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በተጨማሪም “ፍትሕ የለም እንጂ እኔ ነጻ ሰው ነኝ። ፍርድ ቤቱ በነጻ ለቆ ለደረሰብኝ በደል ሁሉ ካሳ ሊያሰጠኝ በቻለ ነበር” ብለዋል።
ሁለተኛ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ ናቸው። እሳቸውም “በዚህ ችሎት የቀረብኩት እና ለ550 ቀናት በግፍ እና በጭካኔ እገታ ውስጥ የምገኘው ለአንድ ደቂቃ እንኳን በጥፋተኝነት የሚያስቀጣ የሕግ መተላለፍ ስለፈፀምኩ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የሕልውና ጥያቄዎች በይፋ በማቅረቤ፣ በሕዝብ ላይ የሚፈፀምን ግፍና በደል በማስረጃ በመሞገቴ ነው” ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈፀሙ ተናግረዋል።
አቶ ክርስቲያን በመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት በነበራቸው ኃላፊነታቸው “ተደጋጋሚ የአመራር ብልሹነት” ያሳዩ አካላት ላይ “የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” ክስ እንዲመሠረት ፍትሕ ሚኒስቴርን ማዘዛቸውን አስታውሰዋል። በዚህም ሳቢያ ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ሦስተኛ ተከሳሹ ሆነው የቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገርም “እኔ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ነኝ። የወከለኝን ሕዝብ ሰቆቃ እና ስቃይ በምክር ቤት ውስጥ በመናገሬ ነው የተከሰስኩት” ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠት የተከሰሱበትን ወንጀል አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ችሎት የቀረቡት 16 ቱም ተከሳሾች በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተብን ክስ “የሀሰት ነው፣ ወንጀሉንም አልፈፀምንም” ብለው መከራከራቸውንና ቀጥሎም ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ይዞ ቀርቦ ለችሎቱ ለማሰማት ቀጠሮ በመጠየቁ ሂደቱ መጋቢት 5 አስከ 12/2017 ዓ.ም. እንዲቀጥል ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልል እና የፌደራል ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ፖለቲከኞች በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው ከ11 ወራት በፊት መጋቢት 18/2016 ዓ.ም. ነበር። አስ