ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “የጊዜያዊ አስተዳደሩ በሶስት ጀነራሎች ላይ ያሳለፈው የእግድ ውሳኔ ተቋማዊ አሰራርን እና ህግን ያልተከተለ ነው” - የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ በተለያዩ ግንባሮች አዛዦች መሆናቸው የተገለጸ ሶስት ጀነራሎችን በግዜያዊነት ማገዳቸውን አስታወቁ፤ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ እግዱ ተቋማዊ አሰራርን እና ህግን ያልተከተለ ነው ሲል ገልጿል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መግባባት እስኪደረስ በሚል ጊዜያዊ ዕገድ እንደተላለፈባቸው በደብዳቤ ያስታወቋቸው ጀነራሎችም፤ ሜጀር ጀነራል ዮሃንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጀነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ ናቸው።

በፕሬዝዳንቱ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ጀነራሎቹ በግዜያዊነት የታገዱት “ከመንግስት ውሳኔ ውጭ መላ የክልሉን ህዝብ እና ወጣቱን ወደ ግርግር፣ የጸጥታ ሀይሉን ወደ  እርስ በርስ ግጭት የሚያስገባ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ በመሆኑ ነው” ብሏል፤ የጀነራሎቹ እንቅስቃሴ “ህዝቡ ወደማይወጣው አዘቅት የሚከት ነው” ሲል አስታውቋል።

የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ “የወንጀለኞች ጠበቃ መሆን ይብቃ” በሚል ርዕስ ዛሬ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን እንደማይቀበለው አስታውቋል፤ “የእግድ እርምጃ የተላለፈው በወንጀለኞች ላይ የተግባር እርምጃ መውሰድ ስለተጀመረ ነው” ብሏል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ በሶስት ጀነራሎች ላይ ያሳለፈው የእግድ ውሳኔ “ተቋማዊ አሰራርን እና ህግን ያልተከተለ ነው” ሲል ገልጿል።

“ያልሾመውን ያወረደ ነው” ሲል የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ውሳኔ የገለጸው የጸጥታ ሀይሉ መግለጫ ‘በግል የተወሰደ እርምጃ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን ስልጣንን ተጠቅሞ ወንጀልን እና ወንጀለኞችን ለመከላከም እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ በመሆኑ ሊቆም ይገባል” ሲል ጠይቋል።

“የተጀመረው ህግ እና ህገመንግስቱን የማስከበር ስራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ለህዝባችን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተመሳሳይ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ባወጣው መግለጫ የጉዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ውሳኔን ህገወጥ ሲል ኮንኗል፤ “የትግራይ ሰራዊትን ለማፍረስ ሲያደርግ የነበረው ሴራ ወደ ከፍተኛ እና አደገኛ ደረጃ አሸጋግሮታል” ሲል ገልጿል።

“የቀድሞ ፕሬዝዳንት” ሲል ቡድኑ በመግለጫው የጠራቸው አቶ ጌታቸውን “ከተሰጣቸው ስልጣን እና ሃላፊነት ውጭ በጀነራሎቹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጥረዋል” ሲል ተችቷል፤ እግዱ ምንም አይነት መሰረት የሌለው እና ሊገበር የማይችል ነው ሲል ገልጿል።

“የሰራዊቱ የእዝ ሰንሰለት በባህሪው ለቅጽበት እንኳ ሊቋረጥ አይገባውም” ያለው የቡድኑ መግለጫ የግንባር መሪዎችን አግጃለሁ ማለቱ በራሱ ሆን ተብሎ ተጋላጭነትን እንዲጨምር የሚያደርግ፣ የትግራይን ሉዓላዊነት እና የህዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ ክህደት ነው” ሲል አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button