
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም፡- ግጭቶች በቀጠሉበት የአማራ ክልል ውስጥ በአበባ እና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርቶ የነበረው ሴሌክታ ዋን የተሰኘው የጀርመኑ ኩባንያ ክልሉን ጥሎ መውጣቱን እና ስራዎቹን ወደ ኬንያ እና ኡጋንዳ ማዛወሩን አስታውቋል።
ኩባንያው እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረሱ የጠቀሰው ዋነኛ ምክንያት “ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እና ወታደራዊ ውጥረት የበዛበት አካባቢ” በመሆኑ ነው ብሏል።
ኩባንያው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ከምትገኘው ኩንዝላ ከነበረው ቦታ ወደ ኬንያ እና ኡጋንዳ መዛወሩ ከአንድ ሺ በላይ የስራ እድሎች እንዲቀሩ ማድረጉን አመላክቷል።
ኩባንያው በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩት ዋና ዋና የሎጂስቲክስ ችግሮች አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በቋሚነት ሊፈቱ እንዳልቻሉ ገልጾ ‘በኢትዮጵያ ስራውን ለማቋረጥ የደረሰበት ውሳኔ በጥንቃቄ የታሰበበትና በመጨረሻም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘ መሆኑን ጠቁሟል።
መግለጫው አክሎም “ከሁሉም በላይ የሰራተኞች ደህንነት በሚፈለገው መጠን ሊረጋገጥ የሚችልበት ምንም አይነት ዋስትና የለም” ሲል ገልጿል።
የሴሌክታ ዋን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አንስጋር ክሌም በሊንክድኢን ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ውሳኔውን “ለመዋጥ የሚከብድ መራራ ክኒን” ሲሉ የገለጹት ሲሆን “እድገት ከታየበት የጥቂት አመታት ስራ በኋላ በኩንዝላ ያለውን የምርት ቦታችንን ለመዝጋት ተገደናል” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ስራ አስፈጻሚው አንስጋር ክሌም የኩባንያውን ጥረት በማስታወስ “በቦታው ላይ ከነበረው ቁርጠኛ ቡድን ጋር በመሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዓታት ኢንቨስት ያደረግንባቸው፣ እውቀት የገነባንባቸው እና በህዳር 2022 የእርስ በርስ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የተሻለ የወደፊት ተስፋ ያደረግንባቸው ዓመታት ነበሩ፤ ሆኖም፣ የፖለቲካው አለመረጋጋት ሊታለፍ የማይችል እንቅፋት ፈጥሮብናል” ሲሉ አክለዋል።
በተጨማሪም ውሳኔው ከአንድ ሺ በላይ የስራ እድሎችን እንደሚያስቀር፣ እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ እስከ 10ሺ የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ ገልፀዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ከዚህ ቀደም በነሀሴ 2015 ዓ.ም በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከሶስት ሺ በላይ ቋሚ ስራዎች መቋረጣቸውን እና በኢንዱስትሪዎች ላይ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ማጋጠሙን መዘገቡ ይታወሳል።
በተለይ የአበባ፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ልማትና ገበያ ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች በተለይ እንደተጎዱ ዘገባው አመልክቷል።
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየካሄዱ ያሉት በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች በተለይ በቅርብ ወራት ውስጥ ተባብሰው ቀጥለዋል።
ለአብነትም በዞኑ ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጅማት እንቆቅማ ቀበሌ አርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከለ በተካሄደ “በከባድ መሳሪያ” በታገዘ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊ እና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገን ዘግበናል።
በግጭቱ ከደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በተጨማሪ በርካታ የሰብል ምርቶች መቃጠላቸውን ዘገባው አመልክቷል። አስ