
የትግራይ ክልል ዋነኛ የጦር አውድማ የመሆን አደጋ ተጋርጦበታል ብለዋል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2017 ዓ.ም፡- ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ “በማንኛውም ጊዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል” ሲሉ አፍሪካ ሪፖርት በተሰኘ መጽሔት ባሰፈሩት አስተያየት አስጠነቀቁ።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለቱ አገሮች አልፎ ሱዳንንና የቀይ ባህር አከባቢዎችን ሊያጠቃልል ይችላል ያሉት ጄኔራሉ “ትግራይ ከእንዲህ አይነት ግጭት እርቃ ሰላምን ማስፈን ትመርጣለች” ሲሉ ገልጸዋል፤ ነገር ግን “የሰላም አማራጭ እያጠበበ በመምጣቱ ጦርነት ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ሊቀር ይችላል” ሲሉ አክለዋል።
አያይዘውም አዲስ አበባና አስመራ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ጥምረት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ “በቀጣይነት እያሽቆለቆለ” በመምጣቱ ጦርነት የመቀስቀስ ዕድሉ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል።
“ዝግጅቶች የመጨረሻው ደረጃ ላይ ናቸው። ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት አንድ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደኋላ መመለስ ይከብዳል” ብለዋል።
በተጨማሪም ኤርትራ “ጠብ አጫሪ ሀገር ነች” ሲሉ በመግለጽ በዙሪያዋ ያሉትን አገሮች በተለይም በኢትዮጵያን እና በሱዳን ያለውን አሁናዊ ሁኔታ ለመጠቀም እየሞከረች ነው ሲሉ ከሰዋል።
አክለውም ኤርትራ ትግራይን ለምኞቶቿ አለመሳካት “ዋነኛ እንቅፋት” አድርጋ እንደምትመለከታት የጠቆሙት ጄነራሉ ኢሳያስ በትግራይ ላይ ማሳካት የፈለጉተን ሳያሳኩ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ መቆሙን ተከትሎ “ተኮሊፍና” ሲሉ የገለጹት ለእሳቸው ያልተቋጨውን ጦርነት ለማጠናቀቅ አስመራ እያዘጋጀች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ውስጥ ያለው ክፍፍል ሁኔታውን የበለጠ ሊያወሳስበው እንደሚችል ጠቅሰው “ያለፉትን እና የአሁኑን ጥፋታቸውን ለመሸፈን የሚፈልጉ በህወሓት ውስጥ ያሉ አካላት ከተጠያቂነት ለመትረፍ እና እራሳቸውን ለማዳን ከኢሳያስ ጋር መተባበርን ሊመርጡ ይችላሉ” ብለዋል።
አንዳንድ የትግራይ መሪዎች ኤርትራን አብይ አህመድን ለማስወገድ እንደ መሳሪያ አድርገው እንደሚመለከቷት ጠቁመዋል።
ጄኔራል ጻድቃን ዳግም የሚቀሰቀሰው ጦርነት “አስከፊ መዘዞች” እንደሚኖሩት ገልጸው “ጦርነቱ ሲያበቃ አሁን በአከላለል የምናውቃቸውን ሀገራት ላናገኛቸው እንችላልን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በተለይም ዓለም አቀፋዊ ትኩረቱ እንደ ዩክሬን፣ ሩሲያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሉ ሌሎች ቦታዎች ላይ ያተኮረ ሆኖ ከቀጠለ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ አዳዲስ የፖለቲካ አሰላለፎች እንደሚኖሩ ተንብየዋል።
ጻድቃን ትግራይ ያላት አማራጭ “ጦርነትን ማስቀረት” እና “የፕሪቶሪያን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መግፋት” እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለምአቀፍ አጋሮች “በአስራ አንደኛው ሰአት ሌላ አሰቃቂ ጦርነት ለማስቀረት ጣልቃ እንዲገቡ” አሳስበዋል።
ሆኖም ግን ጦርነትን የማስቀረት ጥረት ካልተሳካ፣ በሁሉም መንገድ በወታደራዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አካሄድ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማቆም ለትግራይ እና ለክልሉ የተሻለ ጥቅም ነው ብለዋል። አስ